Bete Amhara

Bete Amhara

Monday, November 30, 2015

አማራ ነኝ እንጅ!!!!!
ከማረሻው ግርጌ፣ ከቀንበሩ ገመድ፣
ከበሮቼ ጋራ፣
ከጥቁር አፈር ጋር፣
አብሬ እምወጣ፣ አብሬ የምወርድ፣
አንበሳን ታግዬ፣
እንደ ፈረስ ወገብ፣ ቼ ብዬ የማለምድ፣
ሰማዩን አምኜ፣
ስለት የማስገባ፣ ለታቦቴ እምሰግድ፣
አማን አርገኝ ብዬ፣ ለጀማው እማረግድ፣
ምጣድ ያመሰውን፣
የጋመ ባቄላ፣
እንክክ እንክክ ብዬ፣ እጄ ላይ የማበርድ፣
አማራ ነኝ እንጅ፣
መንገድ ሰፋኝ ብዬ ፣
መንገድ ከገባ ጋር፣ ተነስቼ እማልነጉድ።
አማራ ነኝ እንጅ፣
መሬቱን አምኜ፣
አማን ኢማን ብዬ፣
ባንተው ይሁን ብዬ፣
ባንተው መጀን ብዬ፣አይኔን የማቀና፣
የጎረቤት ማጀት፣
ለምን ሞላ ብዬ፣ በሰው የማልቀና፣
ከወንድሞቼ ጋር፣
ከዘመዶቼ ጋር፣
በሌማት የምጎርስ፣ ንጣይዋን እንጀራ።
አማራ ነኝ እንጅ፣
አባይ ባጠገቤ፣ አቅፎ የሚስመኝ፣
ጣና በትንፋሹ፣ ባይኑ የሚጠቅሰኝ፣
ጎተራ እንደሁ እንጅ፣
ለወንድሞቼ ራብ፣ ማዴ የማያንሰኝ።
ልጄን በወገቤ በአንቀልባዬ አዝዬ፣
በአገልግል በሰንሰል፣
የሻገተ እንጀራ፣ ጣቢታ አንጠልጥዬ፣
ጎጆዬን ያቀናሁ፣
ቀን ከቀበሮ ጋር፣
ማታ ከጅብ መንጋ፣ ከድብ ጋር ታግዬ።
መታመን የሚሉት፣
መዋደድ የሚሉት፣
የጥቁር አፈር ቃል፣ ልቤ ላይ ተሰርቶ፣
በወንድሞቼ ላይ፣
የተጣደው በደል፣
የሚያብረከርከኝ፣
የሚያብሰከስከኝ፣ ጉልበቴ ስር ገብቶ።
አንበሳ ከጅብ ጋር፣
እኔ እበላ እበላ፣ በሆድ ሲታገሉ፣
አሞራና ውሻ፣
እኔ እግጥ እኔ እግጥ፣
እየበጣጠሱ፣ እየዘለዘሉ፣
በአጥንት ተናጭተው፣ በስጋ ሲጣሉ፣
አንተም ስጥ፣
አንተም ስጥ ፣
ብየ የማስታርቅ ፍቅር የሚርበኝ፣
እኔ ነኝ አማራ፣
እንኳንስ ወንድሜ፣
አራዊት ጫካውን፣
ድካውን ሲነጥቁት፣ የሚያንገበግበኝ።
አኔማ አማራ ነኝ፣
ሰማይ ከዳ ብዬ፣
ምድር ጦፈች ብዬ፣
የከሳው በሬዬን፣ አርጀ እማልበላ፣
ነገ አለልኝ ብዬ፣
የዘር ጃምዮየን፣
ላንዲት ርሃብ ብዬ፣ በእሳት የማልቆላ፣
በቂጣ የማልሽር፣
የአባቶቼን ግዝት፣የአባቶቼን ማላ።
አዎን አማራ ነኝ፣
ስሜ የጠገበ፣
ማርና ነጭ ጤፍ፣ ጮማና ብርንዶ፣
ባልበላም በልተሃል፣
ባልተኩስ ገድልሃል፣
ተብዬ እምጠራ፣
ተብዬ እምፈለግ፣ ፍርደኛ አጋሚዶ፣
አቤት ባይ ባተሌ፣
በሸንጎ በቀዬው፣ ስሜ ፍርድ ለምዶ።
አማራ ነኝ እኔ፣
ደብረ ግሸን ከርቤ፣
ረጅም መቋሚያ፣
እጀን ተደግፌ ታቅፌ እምወጣ፣
እንኳን የገዛ እጄን፣
አሳልመኝ ያለኝን፣
አይዞህ እያልኩኝ፣ ደግፌ እማመጣ።
አማራ ነኝ ጓዴ፣
ከጥማድ እርሻዬ፣
አምላክ የሰጠኝን፣
ጥንቅሽና ውልቢኝ፣
አሻግሬ እያየሁ፣ ማማ ተቀምጬ
አላፊ አግዳሚውን፣
ቅመሱልኝ የምል፣ ከእርሻዬ ቆርጬ።
አማራ ነኝ አዎ፣
በደረቅ ባቄላ፣በእንኩሮ መቀጣ፣
ጣዬ ሲበዛብኝ፣
ገብስ ቆሎዬ ላይ፣
ጉሮሮየን ላረጥብ፣ጠላ የምጠጣ፣
ባልበላሁት ዝልዝል፣
ባልጠጣሁት ማር ጠጅ፣ ሰክሬ እምወጣ።
በኩርማን እንጀራ፣
በድሪቶ ጋቢ፣
በእራፊ መቀነት፣ አንጀቴ ተሳስራ፣
በልቶብናል አሉኝ፣
የወንዙን እንጎቻ፣ ያገሩን እንጀራ።
ምነው ሆዴን ባዩት፣
ምነው ጎተራዬን፣ባዩት ወንድሞቼ፣
ይገባቸው ነበር፣
እነሱን ያቀናሁ፣
እነሱን ያጠገብኩ፣እኔ ተራቁቼ።
ከቶ ምን በድዬ፣ምን አድርጌያቸው ነው፣
ኧረ መጥተው ይዩኝ፣
እህል የጓሸበት፣
ወንድም የተራበ፣ ሆዴ እኮ ባዶ ነው።
ውሃ ጠማኝ ብዬ፣
ሃሩር በላኝ ብዬ፣ ከመንገዴ አልወጣ፣
እኔ አይደለሁም ወይ፣
እፍኝ ውሃ ጠምቶኝ፣
ለእኒያ ወንድሞቼ፣ ባህር የማጠጣ።
በጭብጨባ ብዛት፣
በምርቃት ግሳት፣
ሞቅ ሞቅ አይለኝ፣ወደላይ አልወጣ፣
በእርግማን ውርጅብኝ፣
በስድብ ነበልባል፣
ተሰደብኩኝ ብዬ፣ ወደ ታች አልመጣ።
ከላይ ነኝ አላልኩህ፣
ከታች ነኝ አላልኩሽ፣ አለሁ በእኩሌታ፣
ማነው የሚሰፍረኝ፣
ማነው የሚያጉድለኝ፣
ከባንዲራው ቀለም፣ ከባቶቼ ቦታ።
አዎን አማራ ነኝ፣
ጦቢያ የምትባል፣
የነፃነት ሰንደቅ፣
ያኔ ስትበጃጅ፣ ያኔ ስትሰራ፣
አንድ ላይ ሲማገር፣ የቤቷ ወጋግራ፣
እኔ አይደለሁም ወይ፣
ውሃ ልኳን ያቆምኩ፣ ወንድሞቼ ጋራ፣
እንዴት እጎድላለሁ፣
ካስቀመጡኝ መንበር፣ ካስቀመጡኝ ስፍራ።
አዎን አማራ ነኝ፣
የፈረሰ ማገር፣
የፈዘዘ ወራጅ፣
የዛለ ምሰሶ፣
እንደገና እንስራ፣
እንትከል እያልኩኝ፣
የደለቅኩት ድቤ፣
ከተሰማ ባገር፣
ከሞቀ በዃላ፣
በጅጌ በደቦ፣ በቀየው ታውጆ፣
አዳ ምን ዋጋ አለው፣
ሁሉም ሳር ይመዛል፣
ያድርበት ይመስል፣
በገፈፈ ክዳን፣ በዘመመ ጎጆ።
እረ እኔ አማራ ነኝ፣
የቦዘኔ ቃሪያ፣
የጤፍ ዱቄት ቂጣ፣
የሳማ ነጭ ወጥ፣"
የማሽላ ቆሎ፣
እንጀራ ነው ብዬ፣
እየገረገረኝ ቆርሸ፣ እምበላ፣
ጮማ ነው እያሉኝ፣
ቅቤ ነው እያሉኝ፣
ማጀቴን ያላዩ፣ ሰምቶ አዳሪ ሁላ።
አዎን አማራ ነኝ፣
አሳድረኝ ብሎ፣
ቁራሽ ስጠኝ ብሎ፣ከመጣ ከኔ ቤት
አልጋዬን የምለቅ፣
ቁልፍልፍ ብዬ፣
መደብ እምተኛ፣ በታበሰ ማጀት፣
ጦሜን የምተኛ፣
በባዶ ማድጋ፣ በተቋጠረ አንጀት።
ታዲያ እኔ ነኝ ባዳ??
እኔ ነኝ ባይተዋር???
በወንድሞቼ ደጅ፣
ሚዛን ያጎደለኝ፣ ለአይናቸው ቀልዬ፣
በአባቶቼ ማጀት፣
ሰርክ የምገፈተር፣
ና ውረድ ና ግባ፣ ና ውጣ ተብዬ።
የአባቶቹን ሃገር፣
የአርበኞቸን ርስት፣
ያንተ ቤት አይደለም፣
እያሉ ዘበቱ፣
በሽሙጥ አይናቸው፣ አባረሩኝ በቃ፣
ባዶ እጄን ሰደዱኝ፣
ያለ ስንጥር አፈር፣ ያላንዲት ጦሪቃ፣
ገፈተሩኝ ጓዴ፣
ሰው አላየም ብለው፣
በጠቆረው ሰማይ፣ ሌት በጠፍ ጨረቃ።
ይስሙ ንገሯቸው፣
ከነ ሻሾ በረት፣
ከነ ላሎ ማጀት፣
ሺ ጊዜ ቢታለብ፣ ማለቢያው ቢሞላ፣
ለስሙ ነው እንጅ፣
ፈርዶብኝ ነው እንጅ፣
በአዋዜ አይደለም ወይ፣
በእሬት አይደለም ወይ፣
ከወንድሞቼ ጋር፣ ፈትፍቼ እምበላ፣
አዎን፣
ከባዶ ሌማት ላይ፣
ከዱባ መረቅ ላይ፣
ዘመን የሚሻገር፣
እንቅብ የሚሞላ፣
ጣቢታ እየጋገርኩ፣ ተአምር የምሰራ፣
እኔ ነኝ ባንዲራው፣
እኔ ነኝ ሰንደቁ ፣
እኔ ነኝ፣ እኔ ነኝ፣ እኔ ነኝ አማራ።
ገጣሚ:- መንግስቱ ዘገዬ (ጃኖ መንግስቱ)
ከ ደሴ

https://www.facebook.com/permalink.php?story_fbid=923622881018470&id=808909555823137