Bete Amhara

Bete Amhara

Friday, June 26, 2015

አማራ ሁሉ ወደ ጎበዝ አለቃነቱ ይመለስ!
--------------------------------------
አባቶቻችን የጎበዝ አለቃ የሚባል የመንግስትን ውድቀት ተክቶ አገር የሚያረጋጋና ወደሰላም የሚያሸጋግር አሰራር ነበራቸው፡፡ አንድ ንጉስ ሲወድቅ ወይም አካባቢያዊ ገዥዎች በጦርነትም ሆነ በሌላ መንገድ ሲወድቁ አገር እንዳትታመስ እና ህግ እንዳይፈርስ በሚል ብሂል የጎበዝ አለቃ የሚባለው አሰራር ወዲያው ተግባር ላይ ይውላል፡፡ የጎበዝ አለቃ ተብሎ የሚመረጠውም በአካባቢው ጥሩ ስምና ዝና ያለው፤ ፍትህንና ርትእን የሚያውቅ፤ ታማኝ፤ ታዛዥ፤ ጨዋ እና ጀግና የሆነ ሰው ነበር፡፡ ይህንን የሚያሟላ ሰው በአካባቢው ይመረጥና ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ይሆናል፡፡ ህዝቡም በዛ ጎበዝ አለቃ ሀላፊነት አመራር ስር ይገባል፡፡ በዚህም አሰራር አገር አይፈርስም፤ ህግ አይጓደልም፤ ሰላም አይናጋም ነበር፡፡ ይህ የገነገነ የአማራ ስልጡን ባህል ነው፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ ከ1960ዎቹ ትውልድ በፊት የነበረው አማራ በአለቃ የሚያምን ነበር፡፡ በተዋረድ የበታቹ የበላዩን ፈጽሞ እያከበረውና በትህትና እየታዘዘው የመንግስትንም ሆነ ሌላ ስራ ይሰሩ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን በዘመናዊ ትምህርት ሰበብ የተሰበረው ያ ጨዋና ተዋረዳዊ የክብብር ስርአት በግድ መመለስ አለበት፡፡ አባቶቻችን ለቁጥር የሚታክተውን ውጫዊና ውስጣዊ ጠላት አንበርክከው እኛን ክብር ያለን ሰዎች እድንሆን ያደረጉን እርስ በእርስ በነበራቸው ጠንካራ ተዋረዳዊ መከባበር ነው፡፡ የበላዩ የበታቹን በፍጹም ትህትናና ታማኝነት ይመራል፡፡ የበታቹም በፍጹም ቅንነት፤ ትህትናና ታማኝነት ይታዘዛል፡፡ የእርሱም የበታች እንደዛው ያደርጋል፡፡ በዚህ መልኩ በስርአት ኖሩ፡፡ ያንን ስርአትም በወጉ ሳንረከብ መሀል ላይ በምእራባዊያን ትምህርት የተዋጀው ትውልድ መጣና እርስ በእርሱ ተጠፋፍቶ የአያትና የልጅ ልጅ ትስስሩን ድልድይ ሰበረው፡፡ እኛ ደግሞ የተሰበረውን መጠገን እና የተበላሸውን ማስተካከል ግዴታችን ነው፡፡ እንደዛ ስናደርግ የአማራን ባህል ወደነበረበት የስርአት ምልአት እንመልሰዋለን፡፡ አሁንም ከተደቀነብን የጥፋት አደጋ የምንተርፈውና አማራነታችንን እንዲለመልም የምናደርገው የአባቶቻችን መንገድ ከዘመናዊው ባህል ጋር አጣምረን እና አስማምተን ስንጓዝ ብቻ ነው፡፡ እርስ በእርሳችን በመመካከር ከመካከላችን ሻል ያለውን አማራ እየመረጥን የየራሳችንን ትናንሽ በጎበዝ አለቃ የሚመሩ ድርጅቶች እንፍጠር፡፡ የጎበዝ አለቃ እየመረጥን በመረጥነው የጎበዝ አለቃ አመራር መስመር እንግባ፡፡ የአባቶቻችንን መንገድ እንከተል፤ መንፈሳቸውንም እንውረስ፡፡ በዚህ መንገድ ብቻ ነው የምንድነው፡፡ ሁሉም አማራ አምስትም ሰባትም እየሆነ ጥብቅ ጓደኝነት ይመስርት፡፡ ይነጋገር፡፡ ይስማማ፡፡ ይውስን፡፡ የጎበዝ አለቃውን ይምረጥ፡፡ የጎበዝ አለቃው በፍጹም ታማኝነት እና ጀግንነት የመረጡትን ወንድምና እህቶቹን ይምራ፡፡ በጎበዝ አለቃው የሚመሩት በፍጹም ታማኛነት እና ቅንነት ለአለቃቸው ይታዘዙ፡፡ አባቶቻችን ከደረሱበት የምንደርሰው አባቶቻችን በሄዱበት መንገድ ስንሄድ ነው፡፡ አባትህ በሄደበት መንገድ ሂድ…አባትህን ሁን…..የአማራ ልጅ፡፡
ድል አማራ!
መለክ ሐራ ከቤተ አማራ