Bete Amhara

Bete Amhara

Monday, June 15, 2015

ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌን የምታገኙ ይሄንን ንገሩልኝ
አማርኛ ተናጋሪና የእርቅና የተራድኦ ድርጅት ብሎ ድንግርግር
===============================
መቸም እኔ አንድ ብላቴና ነኝና ለእርስዎ አማራን በሚያክል ትልቅ ህዝብና በገጠመው አንገብጋቢ ጉዳይ ሳቢያ የተሰማኝን መጻፌ ከማንጓጠጥ ቢቆጠርብኝ እሽ ብየ እንደምቀበል ማመን እወዳለሁ፡፡ ሁለት ጊዜ በጻፉት ላይ የተሰማኝን ልናገር፡፡ በመጀመሪያው ጽሁፍዎ ትልቅ ቁም ነገር የሚሆነው የአማራን ጉዳይ ደፍረው ርእስ ሰጥተው መጻፍዎ ብቻ ነው፡፡ የተቀረው ሀሳብ አካዳሚያዊና ከወቅቱ መሰረታዊ ችግር በብዙ መልኩ የራቀ ነው፡፡ ጉዳዩ አሳስቦዎት መጻፍዎ የሚደነቅ ይሁን እንጅ የጽሁፉ መነሻና ግብ-ጥቆማ አማራን በአሁኑ ወቅት ከገጠመው ችግር የራቀ ነው፡፡ የእርስዎ ዋናው ሀሳብ አማራ የእርቅና የተራድኦ ድርጅት ያቋቁም ነው፡፡ ምናልባት አማራ አሁን ያለበትን ሁኔታ ያልተገነዘቡት መሰለኝ፡፡ እውነታው እንዲህ ነው፡፡ አማራ በአሁኑ ሰአት የእርቅም ሆነ የእርግማን ሀሳብ ይዞ ቢመጣ ማንም የሚሰማው የለም፡፡ ለምን ቢባል ሰይጣን ውዳሴ ማርያም ስለደገመ ቤተ መቅደስ ገብቶ ይቀድሳል ማለት አይቻልም፡፡ በሁለተኛው ጽሁፍዎ እንደጠቀሱትና እኔም እንደምለው ላለፉት 40 አመታት በአንድም በሌላ መንገድ የኢትዮጵያ ዘውጌ ብሔረተኞች ዋና ስራቸው አማራን ዲያብሎስ አድርጎ ማሳየትን ነው፡፡ ስለዚህ አንድ መናኝ ከአምላክ በዲያብሎስ በኩል የተላከለትን ህብሰት ይብላው ወይስ ይወርውረው የሚል መስቀለኛ ጠርዝ ላይ ያስቀምጣል፡፡ የእርቅና የተራድኦ ድርጅት ሲሉ አማራው ይህንን ድርጅትና አላማ የሚያደርሰው ለአማራው ነው ወይስ አማራን በዲያብሎስነት ለሚመለከተው ለሌላው ብሄረሰብ ነው? የሚሰማ ሳይኖር ስለምንም ነገር መናገር አይቻልም፡፡ እኔ እንኳን በእድሜየ በደረስኩበት አማራ የተባለ ሰው ያመጣው ሀሳብ የነፍጠኛና መሰል ተቀጽላ ስሞች እየተሰጠው ሲንቋሸሽ እና ሲብጠለጠል ነው የማውቀው፡፡ ከልምድ እንደተረዳሁት አማራ ያመነጨው ማናቸውም ሀሳብ በሀሳብነቱ ሳይሆን በአማራነቱ ነው የሚመዘነው፡፡ ይህ በድርጅቶች ብቻ የሚደረግ እንዳይመስሎዎት፡፡ በእያንዳንዱ ግለሰብ ላይ የሚንጸባረቅ በተዋረድ አገር አቀፋዊ ችግር የሆነ እንጅ፡፡ ስለዚህ ሰሚው የማይሰማው ተናጋሪ ባይናገር ይሻለዋል፡፡
ሁለተኛው የጽሁፉ ጭብጥ ተራድኦ ድርጅት ያሉት ነገር ነው፡፡ ተራድኦ ድርጅት ሲሉ አማራን እንደምን ቢስሉት እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ድርጅቱ ማንን ምን ብሎ፤ ለማን ምን አድርጎ፤ በምን መንገድ አማራን ከጥፋት መታደግና በኢትዮጵያ ውስጥ ሊኖረው የሚችለውን ሚና በቦታው ማሰቀመጥ እንደሚችል በውል አላሳዩም፡፡ ደግሞስ ተራድኦ ድርጅት መመስረት እንዴት ቅድሚያ ጉዳይ ሊሆን እንደቻለ ምንም የሰጡት ማብራሪያ የለም፡፡ እንደኔ እንደኔ ግን ሌሎች መደረግ ያለባቸውን አማራጮች አንድ በአንድ አስበውባቸው ይሄው የተራድኦ ድርጅት ጉዳይ የበለጠ አሳማኝና በቀላሉ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ነው ብለው አምነውበት ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ እንደሚገባኝ የተራድኦ ድርጅት የሚያቋቋም ግለሰብም ሆነ ቡድን እንቅስቃሴው ሊደረግበት በታሰበው ቦታና ሁኔታ ውስጥ በሚኖረው ጫናና ሚና ይወሰናል፡፡ አማራ በአሁኑ ሰአት በተራድኦ ድርጅት ነገሮችን መለወጥ የሚስቸውለው ቦታና ሁኔታ ላይ ስላለመገኘቱ በደንብ ያሰቡበት አልመሰለኝም፡፡ የተራድኦ ድርጅት አቋቋሞ የእርቅ ስራ የሚሰራ ግለሰብም ሆነ ቡድን ላቅ ያለ ወይም እኩላዊ ሚና ሊኖረው ይገባል፡፡ ከዚህ በተጻራሪ አማራው ለእርቅ የሚሄድባቸው ብሄረሰቦች በማናቸውም ረገድ ከአማራው የተሻለ ቦታና ሚና ያላቸው ናቸው፡፡ ይህም የእርስዎን ሀሳብ ተቀባይነቱን ፈተና ውስጥ ይጥለዋል፡፡ ከዚህም አንጻር ስናየው አማራው ማቋቋመ ካለበት የተማጥኖ ድርጅት ወይም በሀይል ራስን የማስከበር ድርጅት ብቻ ነው፡፡ የተራድኦ ድርጅት አቋቁሞ ስለእርቅ ለመናገር ተሰሚት፤ አቅም፤ ህግ ያለበት አገርና መንግስት እና መጠነኛ የመደማመጥ ወይም የመደመጥ እድል ሊኖር ግድ ነው፡፡ በእነዚህና ሌሎች ጉድለቶች የተነሳ ያነሱት ሀሳብ የማያስኬድ ይሆናል፡፡
በሁለተኛው ጽሁፍዎም የእርቅና የተራድኦ ድርጂትን ጉዳይ ደግሞው አንስተዋል፡፡ ከላይ የተገለጸው ሀተታ ይህንንም የሚመለከት በመሆኑ መድገም አላሻኝም፡፡ ከዚህ ይልቅ በሁለተኛውም ጽሁፍዎ መግቢያ ላይ አንድ አማራን እና አማራነትን ሊጎዳ የሚችል አገላጽ ተጠቅመዋል፡፡ በአመዛኙ ጽሁፉን ብውደወም ቅሬታ ተሰምቶኛል፡፡ እርሱም አማራ በዘር የለም በባህል ግን አለ ያሉት ነገር ነው፡፡ አማራ በዘር የለም ካሉ በዘር ነገድ የሆነ ሌላ ማነጻጸሪያ ሃሳብ ማቅረብ ነበረብዎ፡፡ አማራ በዘር የለም ሲሉ ሌሎች ግን በዘር ነገድ ናቸው የሚል አንድምታ ያዘለ ንግግር ነው፡፡ እናም በባህል አማራ አለ ብለው በዘር የተካደውን ወይም የተገደለውን አማራ ነፍስ ለመዝራት ሞከሩ፡፡ የማህበረሰብ ሳይንስ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ነገዶች ወይም ጎሳዎች ባህላዊ እንጀ ደማዊ ወይም ፍጥረታዊ አይደሉም፡፡ ሁሉም የባህል ውጤቶች ናቸው፡፡ በዘር እንደዚህ የሚባል ነገድ የለም፡፡ በተለይም ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ በዘር የሚደረገው ክፍፍል በባህላዊው ተጽእኖ የተዋጠ ነው፡፡ እንደጽሁፍዎ አንድምታ እና እንደ ብዙዎች እምነት ማንም ነገድ የባህል ውጤት መሆኑ እያታወቀ አማራ ብቻ የዘር ሀረጉን ከአዳምና ሄዋን እንዲስብ መጠየቁ በጣም የሚያስገርም ጉዳይ ነው፡፡ ልብ ብለን ብናየውና ይህንን የእርስዎን የባህል ኑባሬ ብንመረምረው አማራ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉትና ከጠፉት ነባር ነገዶች አንዱ ነው፡፡ ወደኋላ ሄዶ አማራ መባል በዚህ እርግጠኛ ቦታና ጊዜ ተጀመረ ብሎ መናገር ያለመቻሉም አንዱ የአማራን ለረጅም ጊዜ የቆየ ነገዳዊ ህልውና የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከአማራ መፈጠር በኋላ እየተሰነጣጠቁ ወይም እየፈለቁ የነገድነት ካባ የደረቡ ብዙ ነገዶች የህልውና ጥያቄ ሳይነሳባቸው ቀደምቱ አማራ ላይ የሚደረገው ዘመቻ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች አማራን ሀይማኖታዊ ስያሜ ለመስጠት ይዳዳሉ፡፡ ይሁንና ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት ስለነበረው አማራ በውል የሚናገሩት ነገር የለም፡፡ አማራ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት ከነበረ እንዴት ከኋላ በመጣው ሀይማኖት ማእቀፍ ስር ሊጠራ እንደቻለ የሚሉት ነገር የለም፡፡ አማራ ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ነው የተከሰተው ከተባለ ደግሞ እንዴት ክርስቲያን የሆነው አገው አማራ የሚል ሀይማኖታዊ ስያሜ እንዳልተጎናጸፈ የሚሉት ነገር የለም፡፡ አማራና እስላም የሚለው ሀይማኖታዊ ገለጣ አገውና እስላም ወይም ክርስቲያን አገውና እስላም ማለት ይሆንን ብለው አልጠየቁም፡፡ እንደዛስ ከሆነ ማን የሚባለው ነገድ ነው ከእስልምና መከሰት በኋላ አማራ የተባለው? ከዛስ በፊት ማን ባል ነበር ይህ ህዝብ?
በሁለተኛው ጽሁፍዎ ያነሱት ሌላው ጉዳይ አሁንም አማራን አማራ ብሎ ከመጥራት የተለመደ የመተናነቅ ነገር ይስተዋልበታል፡፡ አማርኛ ተናጋሪ ብሎ እንደመጥራት መቸም ትዝብት ላይ የሚጥል ነገር የለም፡፡ አማርኛ ተናጋሪ ሁሉ አማራ ከሆነ እንግዲህ 80 በመቶው የኢትዮጵያ ህዝብ አማርኛ ይናገራል፡፡ ስለዚህ ይህ ሁሉ አማራ መሆኑ ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ ይህ አገላለጽ በጣም ችግር ያለበትና አደገኛ ነው፡፡ መቸም እንግለዝኛ ተናጋሪ ሁሉ እንግሊዝ ነው ወይም ዌልስ ነው የሚል ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ በምንም መስፈርት ተናጋሪው ከመነጋገሪያው የሚቀድም ህልውና ነው ያለው፡፡ ከእንግሊኛ በፊት እግሊዞች ነበሩ፡፡ አማራም ከአማርኛ በፊት ነበር፡፡ አማራ የሚባል ህዘዝብ መኖሩ ነው አማርኛ የተባለውን ቋንቋ እንዲፈጠር ያደረገው፡፡ አማራ አማርኛን ፈጠረ እንጅ አማርኛ አማራን አልፈጠረውም፡፡ ለምን ቢባል አማርኛ የነገዱን ስም ይዞ የተፈጠረ ተቀጽላ ነው፡፡ የተወሰነ የአማራ ማንነት ያለው ተናጋሪ ያልነበረው ቋንቋ በምንም መልኩ የነገዱን መጠሪያ ተከትሎ ሊሰየም አይችልም፡፡ ለዚህ ማሳያ ብንወስድ ግእዝ በራሱ ትርጉም ያለው ቋንቋ ነው፡፡ የማናቸውም ነገድ ተቀጽላ መጠሪያ አይደለም፡፡ ምናልባት ወደኋላ ሄደን አግአዝያን የሚባለው ህዝብ መጠሪያ ነው ብለን ካላሰብን በቀር፡፡ እናም አማርኛ ተናገሪ ሁሉ አማራ አይደለም፡፡ አማራን በራሱ ቋንቋ ተናጋሪዎች መሰየም አድሎአዊ ነው፡፡ የአባትን ስምና ድርሻ ቀመቶ ለልጅ ወይም ለሩቅ ዘመድ እንደማደል ይቆጠራል፡፡ በዚህ አካሄድ እኮ አማራ ማለት ራሱ አማራው ሳይሆን በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ አማርኛ የሚናገሩ አማራ ያልሆኑ ነገዶች ማለት ነው፡፡ ይህ ልክ ያልሆነ አረዳድም ነው አማራውን የሚናገርለት የሌለው ያደረገው፡፡ አማርኛ የሚናገር ሁሉ ልክ የአማራን ጉዳይ እንደተናገረ ወይም ወክሎ እንደተናገረ በመቆጠሩ አማራው አፉን ተቀማ፡፡ በራሱ ችግሩን አቤት ብሎ ማስረዳት የማይችል ሆነ፡፡ በከተማ አማርኛ ተናጋሪ ሰዎች አማራው አፉን ተነጠቀ፡፡
መለክ ሐራ ነኝ ከቤተ አማራ