Bete Amhara

Bete Amhara

Monday, June 15, 2015

በመጨረሻም ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ መልስ ጻፉልኝ!
________________________________
እኛ ግን ታድለን! ቤተ አማራ እድለኛ ነው፡፡ ልጅ ከአባቱ ጋር የሚያደርገው ንግግር ብቻውን ብዙ ነገር ይመሰክራል፡፡ እኔ ብላቴና መለክ ሐራ ከታላቁ አባታችን ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ፊት እቆም ዘንድ ምንድን ነኝ፡፡ እንዲሁ እድለኛ ሰው፤ አባት ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ መላው ቤተ አማራ ኩሩ፡ ደስም ይበላችሁ፡፡ እኛ መካሪ አባት የሌለን ትውልድ አይደለንም፡፡ በጣም የሚገርመው እኔ ነኝ ያንጓጠጥኳቸው፡፡ እርሳቸውስ ልብን በምታቀልጥ ትህትና ተናገሩኝ፡፡ ጽሁፋቸውን ሲዘጉ ““ቤተ አማራ” ያልከው ይሻላል ብለህ ነው?” በሚል የይቻላል አይነት ጥያቄ ነው፡፡ እናም ቤተ አማራ ትክክለኛ መጠሪያችን መሆኑን ታላላቆቻችንም ያምኑበታል ማለት ነው፡፡ በቃ ቤተ አማራ ጽኑእ ስማችን ነው፡፡ ግን ፕሮፌሰርን አንድ ቦታ በጣም ያበሳጨኋቸው ይመስለኛል፡፡ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ለትልቅ ሰው የሚበጅ አማርኛ አልመረጥኩ ይሆናልና በውነቱ በደለኛ ነኝ፡፡ እንዴው ዛሬም ሳልናገር የማላልፈው ግን እርሳቸው ከታች እንደሚታየው ስለአማራ ደፍሮ በመጻፍ እኔ የመጀመሪያ አይደለሁም፤ መለስና ፕሮፍ. መስፍን ተነጋግረውበታል አይነት ነገር ብለዋል፡፡ እኔ ግን እነዚህ ሁለት ሰዎች የተነጋገሩት ለምስክርነት ይበቃል ብየ አላምንም፡፡ ሙሉ ንግግራቸው አማራ አለ የለም በሚል ንትርክ ነው የሚያልቀው፡፡ ልክ አማራ የማይዳሰስ ረቂቅ ነገር የሆነ ይመስል አለ የለም ሲባባሉ ማየት እንዴት ያሳቅቃል፡፡ እና እነዚህ ሁለት ሰዎች ስለ አማራ ደፍረው ጻፉ ወይ ተናገሩ ሳይሆን የሚባለው አማራን ደፈሩት ነው፡፡ ከሰውነት ወደ አለ የለምነት ክርክር አወረዱት ማለት ነው፡፡
እንግዲህ አባታችንን እጅግ እያመሰገንኩ የእርሳቸውን ሙሉ ጽሁፍ አንዲትም ሆሄ ሳትቀየር፤ ሳትጨመርና ሳትጎድል አስቀምጫለሁ፡፡ በድጋሜ አመሰግናለሁ፡፡
እርሳቸው ይቀጥላሉ፤
ለአቶ መለክ ሐራ፤
ወጣትነትህን ከመልእክትህ በመረዳት “አንተ” እያልኩ ልመልስ። ስለ ጻፍክልኝ አመሰግናለሁ። “ድንግርግር ያልከውን ብዙ አላብራራህልኝም” እል እነደሆነ ነው እንጂ፥ ወጣት ሆነህ መልስ ሰጠኸን የሚል ግምትስ በአእምሮየ አልመጣም። ለማንም ሰው በምንም ጉዳይ ላይ መጻፍ ድፍረት ሊሆን አይችልም።
1. “በመጀመሪያው ጽሁፍዎ ትልቅ ቁም ነገር የሚሆነው የአማራን ጉዳይ ደፍረው ርእስ ሰጥተው መጻፍዎ ብቻ ነው” ስለ አማራ መናገር ድፍረት አይመስለኝም፤ የመጀመሪያውም አይደለሁም። ብዙ ተጽፏል።
2. “አማራ በአሁኑ ሰአት የእርቅም ሆነ የእርግማን ሀሳብ ይዞ ቢመጣ ማንም የሚሰማው የለም፡፡” ካልተሞከረ፥ ሰሚ ሳይኖር ይቀራል፤ ከተሞከረ ሰሚ ሊኖር ይችላል። ካለመሞከሩ መሞከሩ ይሻላል። “የሚሰማው የለም” ብሎ ሙከራውን መከላከል ተገቢ አይመስለኝም።
3. “በምን መንገድ አማራን ከጥፋት መታደግና በኢትዮጵያ ውስጥ ሊኖረው የሚችለውን ሚና በቦታው ማሰቀመጥ እንደሚችል በውል አላሳዩም፡፡ ደግሞስ ተራድኦ ድርጅት መመስረት እንዴት ቅድሚያ ጉዳይ ሊሆን እንደቻለ ምንም የሰጡት ማብራሪያ የለም፡፡” የምፈልገው መጠኑ እንዲሰፋ ነው እንጂ እርዳታውስ ተጀምሯል፤ የሆነ ያልሆነ ምክንያት እያመጣ የሚያደናቅፍ ሰይጣን እንዳይገጥመው እንጠንቀቅ። ደግሞስ፥ ከምን ጉዳይ ነው ለዕርቅ ድርጅት ቅድሚያ የሰጠሁት? መቅደም ያለበትን ጉዳይ እንዴት ነው ወደኋላ የጎተትኩት? አማራው እያለቀ ነው። ከምን መከራ ላይ እንዳለ አንተም ገልጸኸዋል።
4. “እንደኔ እንደኔ ግን ሌሎች መደረግ ያለባቸውን አማራጮች አንድ በአንድ አስበውባቸው ይሄው የተራድኦ ድርጅት ጉዳይ የበለጠ አሳማኝና በቀላሉ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ነው ብለው አምነውበት ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡” “የምትጽፈው ያላመንክበትን ነው” ማለትህ ነው። ይኸ ቅር ያሰኘኛል። መልስ እንዳልሰጥህም ገፋፍቶኝ ነበር።
5. “አማራ በዘር የለም ካሉ በዘር ነገድ የሆነ ሌላ ማነጻጸሪያ ሃሳብ ማቅረብ ነበረብዎ፡፡” ይኽንን ነጥብ ወድጀዋለሁ። አቶ መለስና ፕሮፌሰር መስፍን በአማራው ጉዳይ ላይ ሲወያዩ (“በዚህ ርእስ ስተች የመጀመሪያው ደፋር አይደለሁም” ያልኩትን አስታውስ) አቶ መለስ፥ “አማራ የሚባል ዘር የለም ካልክ፣ ዘር ላይ የተመሠረተ ጎሳ ወይም ነገድ የለም” ብሎ ነበር። እኔም የምለው እኮ፥ ስለአማራው ብቻ ተናገርኩ እንጂ፥ ይኸንኑ ነው። በዘር የተመሠረተ ጎሳ/ነገድ የለም። የሌለን ከሌለ ጋር ማነጻጸር አይቻልም። ስለአማራው የጻፍኩት፥ የምተቸው ስለ አማራ ስለሆነና “አማራ የሚባል ሕዝብ አለ” የሚሉ ሰዎች ዘርን መሠረት አድርገው ስለሚተቹ ነው።
6. “አማርኛ ተናጋሪዎች” ይኽ ስም የወጣውም “አማራ የሚባል ዘር የለም” የሚለውን አስተሳሰብ ለመግለጽ ነው። ጥሩ ስም አይደለም፤ ግን የተሻለ ስም አልተገኘም። “አፍ መፍቻው አማርኛ የሆነ” የሚልም መግለጫ ተሰንዝሯል። እስቲ አማራጭ አምጣ። “ቤተ አማራ” ያልከው ይሻላል ብለህ ነው?
ከሰላምታ ጋር፤
ጌታቸው ኃይሌ