Bete Amhara

Bete Amhara

Monday, June 15, 2015

የአማራ ህዝብ ትግል ወዴት?
(አያልነሽ ስሜነህ፣ መጋቢት 2007 ዓ.ም. – አዲስ አበባ)
ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያዎች “የአማራ ሕዝብ የመገንጠል ትግል ማድረግ አለበት”፣ “መገንጠል ሳይሆን ለነጻነት እንታገል” በሌላ በኩል ደግሞ “አማራ መገንጠል የሚባል ሃሳብ ካነሳ ዓለም በአፍ ጢሟ ልትደፋ ነው ማለት ነው” የሚሉ ገራገሮችን (8ኛው ሺህ ደረሰ ያሉትን ነው) ውይይቶች እየተከታተልኩ ነው። ሁሉም የሚስማማበት አንድ ጉዳይ አለ – የአማራ ህዝብ የዘርፍ ማጥፋት ወንጀል እየተፈፀመበት እንደሆነ፡፡ ይህንን ለማስቆም በሚኬድበት መንገድ ላይ ደግሞ ዝብርቅርቅ ያሉ አተያዮች አሉ፡፡ እንደእኔ እምነት የጠራ አቋም ለመያዝ የመጣንበትንና ያለንበትን ሁኔታ በሚገባ መረዳት ይጠይቃል፡፡ በዕውቀትና በእውነት ላይ የተመሠረተ አቋም ስንይዝ ካሰብንበት እንደርሳለን፡፡ ስለዚህ ህወሓትና ጀሌዎቹ በአማራ ህዝብ ላይ የከረረ ጥላቻ ያሳደሩት ለምንድነው? ከመቼስ ይጀምራል? ወዘተ የሚሉትን ጉዳዮች በሚገባ ማወቅ ይገባናል፡፡ በዚህ ዙሪያ እኔ የተሰማኝን ማለት ፈለግሁ፡፡ ይህ ጽሑፍ የተሟላ የሚሆነው የአማራ ተወላጆች ስትሳተፉበትና የየድርሻችንን ስናዋጣ ነው፡፡ ጽሑፉ ለሥነጽሑፋዊ ውበት ብዙም ትኩረት ስላላደረገ አንብባችሁ ቁምነገሩን ብቻ በመውሰድ የጋራ ጉዳያችን (Common Core) ላይ እንድናተኩር እጠይቃለሁ፡፡
ሰፊው የአማራ ህዝብ ለዘመናት በድህነት፣ በድንቁርና፣ በጭቆና፣ በርሃብና በስደት እየተሰቃየ ያለ ህዝብ ነው፡፡ ከ24 ዓመት በፊት የነበሩ ገዥዎች ቀጥተኛ በሆነ ተጽዕኖ ሀብቱን ሲዘርፉት፣ ሲንገላቱት፣ ሲያስሩ ሲፈቱት፣ ሲገድሉና ሲሰቅሉት እንደነበር እሙን ነው፡፡ እነዚህ ገዥዎች ከራሳቸው በላይ ማሰብ የማይፈልጉና አምባገነናዊ በመሆናቸው ከመነጨ ባህርይ እንጂ የአማራ ህዝብ የተለየ ጠላት ነው ብለው በማሰብ አልነበረም፡፡ እንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የመከራው ገፈት ቀማሽ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ከህወሓት መራሹ መንግስት መቋቋም በኋላ ያለው ሁኔታ ግን የተለየ ነው፡፡ ህወሓት ከመነሻው ጀምሮ ብሔረ-አማራ ጠላቴ ብሎ በመነሳቱና የጥላቻቸውም ጫፍ ወሰን የሌለው በመሆኑ ከመሳደብ፣ ከማንቋሸሽ፣ ከማሳደድ፣ ከድህነት እንዳይወጣ ሴራ ከመሸረብ አልፎ የአማራን ህዝብ ፈጽሞ ለማጥፋት የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደ ነው፡፡ ሴት ህጻናት መካን እንዲሆኑ እየተደረገ ነው፡፡ ህወሓት ከገባ ጀምሮ እስካሁኑ ሰዓት ድረስ ስጋት ናቸው የሚላቸውን የአማራ ተወላጆች ያለምንም ህጋዊ መሠረት ነጻ እርምጃ እየወሰደ በርካታ ሰዎችን ገድሏል፣ እየገደለም ነው፡፡ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ባለፈው የህዝብ ቆጠራ ውጤት እንዳረጋገጠው 2.4 ሚሊየን የአማራ ህዝብ የደረሰበት ጠፍቷል፡፡ ሀገራዊው የህዝብ ዕድገት ምጣኔ 2.5% (የአንዳንድ ክልሎች እስከ 2.7%) ሲሆን የአማራ ህዝብ ብቻ ግን 1.7% ነው፡፡ ይህ ህወሓት የነደፈው ድምፅ-አልባ ፀረ-አማራ ኒውክሊየር ቦምብ ነው፡፡
ህወሓት (ያኔ ተሓህት) በ1968 ዓ.ም. ባፀደቀው ድርጅታዊ ፕሮግራም ላይ የአማራን ጠላትነት የገለፀው በሚከለተለው መልክ ነበር። (ልብ በሉ፣ የተጻፈው ስለ አማራ ብሔር እንጂ ስለገዥ መደቦች አይደለም፡፡ ጠላት፣ በዝባዥ፣ ጨቋኝ እየተባለ ያለው መላው የአማራ ህዝብ ነው)
“በኢትዮጵያ ያሉት ጭቁን ብሄሮች በተለይ ብሄረ-ትግራይ በጨቋኝዋ ያማራ ብሄር የሚደርስባቸው ተጽዕኖ ከጊዜ ወደጊዜ እየጎላና እየተባባሰ በመሄዱ በብሄሮች መካከል አለመስማማትና መጠራጠርን አስከትሏል። (8-9)
ሰፊው የትግራይ ህዝብ ሥራ አጥቶ በሽርሙጥናና በስደት ወ.ዘ.ተ. ብቻ ሳይሆን በረኃብ፣ በድንቁርናና በበሽታ እየተሰቃየ ይኖራል። እነዚህም ችግሮች ወንጀል እንዲፈጽም ይገፋፉታል። ለችግሩ መሠረታዊ ምክንያት ኢምፔሪያሊዝምና ባላባታዊ ሥርዓት ይሁኑ እጂ ጨቋኝዋ የአማራ ብሄር የምታደርገው የኢኮኖሚ ብዝበዛና የፖለቲካ ጭቆና ታክሎበት ነው። ከዚህም በላይ የሚያኮራው የህዝባችን ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ እንዲዳከምና ተዳክሞ እንዲጠፋ ወይም የአማራ ብሔር የገዥ መደብ ጥቅም እንዲጠብቅ የ፫ ሺ ዓመታት ታሪክና ባህላችን መመኪያቸውና መፎከሪያቸው ሆኖ ይገኛል። ይህ የታሪክ ስርቆት በአንድ በኩል የአማራው ብሔር መፎከሪያ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሰፊው የትግራይ ህዝብ ታሪክ እንደሌለው ሕዝብ እንዲያስቆጥረው የተደረገ የመንግስት መመሪያ ነው። ቢሆንም የትግራይ ህዝብ ቂሙንና ተቃውሞውን በቁጣና በጥላቻ በብዙ መንገድ ደጋግሞ ገልጸዋል። ይህና ይህንን የመሳሰሉ አድሃሪ ድርጊቶች አሁን ያለው ፋሽስታዊ መንግሥትም ስለቀጠለበት ሰብዓዊ ክብሩና መብቱ እስኪመለስለት ድረስ ሰፊው የትግራይ ህዝብ ትግሉን አያቋርጥም። ጨቋኝዋ የአማራ ብሔርም ጭቆናዋ እስካላቆመች ድረስ ህረተሰባዊ እረፍት አታገኝም።(ገጽ 15-16)
የትግራይ ህዝብ ብሔራዊ ትግል ፀረ-የአማራ ብሔራዊ ጭቆና፣ ፀረ-ኢምፔሪያሊዝም እንዲሁም ፀረ-ንኡስ ከበርቴያዊ ጠጋኝ ለውጥ ነው። (ገጽ 18)”
ይህን ፕሮግራም ቀርጾ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ለመመስረት ትግል የጀመረው ህወሓት የአማራ ህዝብ የትግራይ ህዝብ ደመኛ ጠላት እንደሆነ ማስተማሩን ቀጠለ፤ ዘፈናቸው፣ ድራማቸው፣ ግጥማቸው፣ ወዘተ ሁሉ የሚያወሳው ስለአማራ ፈሪነት፣ የትግራይ ተራሮች የአማራ መቃብር እንደሚሆኑ፣ አማራን እንዳይመለስ አድርገው እንደሚቀብሩት፣ ወ.ዘ.ተ. ሆነ። የትግራይ አባቶችና እናቶች “አምሃራ አድጊ’ዩ” (አማራ አህያ ነው) የሚለው ለልጆቻቸው ደጋግመው የሚነግሩት የምሽት ተረት ሆነ።
ህወሓት በዚህ ረገድ የተሳካለት ስለመሆኑ ዓለምሰገድ አባይ የተባለው ኤርትራዊ ግለሰብ “Identity Jilted or Re-Imagining Identity? The Divergent Paths of the Eritrean and Tigrayan Nationalist Struggles” በሚል ርዕስ በ1990 ዓ.ም. በጻፈው ባለ259 ገጽ ጥናታዊ መጽሐፍ በግልጽ አስፍሮታል። የአማራ ተወላጆች ሁሉ ሙሉውን ጥናታዊ ውጤት ማንበብ እንደሚገባችሁ በመጠቆም ለተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይ አብነታዊ ማሳያዎችን ላቅርብ።
ዓለምሰገድ በመጽሐፉ፣ “ከሠላሳ ዓመት አውዳሚ ጦርነት በኋላ እንኳን (የአማራ የበላይነት የሰፈነበት መንግስት ጋር) የደጋው ኤርትራ ህብረተሰብ የትግራዮችን ያህል የከረረ ፀረ-አማራ ስሜት የላቸውም። (ኤርትራውያን) ታሪካዊ (ደመኛ) ጠላታቸው ማን እንደሆነ ተጠይቀው 86% የሚሆኑ የኤርትራ ሰዎች ቱርክ፣ ግብጽ፣ ኢጣሊያ፣ ብሪታኒያ፣ ካሉ በኋላ ኃ/ሥላሴ እና ደርግ በማለት የጠቀሱት በመጨረሻ ደረጃ ነው። … የኤርትራውያን ፀረ-አማራ ስሜት ከትግራዮች ይልቅ ለስላሳ ነው።”
ትግሬዎች ግን ደመኛ ጠላታችሁ ማነው ተብለው ሲጠየቁ 1ኛ አማራ ብለው ጀምረው እስከመጨረሻው አማራ ብለው ይደመድማሉ። ‘ከአማራዎች ጋር ታሪካዊ ጠላትነት ነው ያለን፡፡ አማራዎች እኛን ካላጠፉ አርፈው አይቀመጡም።’ በማለት እንደሚገልጹት ጠቅሶ፣ በመቀጠል “ልክ ሁቱዎች ቱትሲዎችን እንደሚያዩዋቸው፣ ትግራዮችም አማራዎችን መሰሪዎችና አታላዮች (ጨቋኞች) አድርገው ነው የሚያዩዋቸው” ይላል ፀሐፊው።
ዓለምሰገድ ማረጃዎችን ሲጠቅስም፣ “በላይ ካሣ የተባሉ የ75 ዓመት አዛውንት ተጠይቀው፣ ‘ሸዋ! ሸዋ! ሸዋ! ጨካኞች፣ ንፉጎች፣ ሰይጣኖች ናቸው፡፡ ሸዋ? እየውልህ … በእግዚአብሔር የማያምኑ አረመኔዎች ናቸው፡፡ ጨካኝ! ጨካኝ! ጨካኝ! … በ1960ዎቹ ጎሬ በነበርኩ ጊዜ ለምሣሌ አንድ የሸዋ አማራ ነበረ፡፡ ከትግራይ መሆኔ ሲያውቅ ንግግር ዘጋኝ፡፡ ትግራይ መሆንክን ካወቁ ሦሰት ደረጃ ወደኋላ ሄደው ልክ እንደማያውቁህ ይሆናሉ። ጭካኔ? የሸዋ ጭካኔ … የፈጣሪ ያለህ … መገመት አትችልም” ማለታቸውን አስፍሯል።
ፀሐፊው ቀጥሎም “የሚገርመው ነገር ጣሊያኖች፣ ቱርኮች፣ ግብጾች ወይም መሀዲስቶች በአብዛኞቹ ትግራውያን እንደጠላት አልተጠቀሱም፡፡ ታሪካዊ ጠላት ሲባል በትግራዮች አዕምሮ የሚመጣው አማራ ነው። ‘አማራ! ሁሌም ጠላታችን አማራ! ሸዋዎች ሁሌም ያታልሉናል። ሁሌም ሊጎዱን ይፈልጋሉ። ጽንፈኛነታቸው አሁን ላለንበት ሁኔታ ዳርጎናል። እግዚአብሔር ከእነሱ የተሻለ ታጋሽና ቻይ ያድርገን እንጂ።” በማለት በንግግራቸው የጥላቻቸውን ጫፍ ያሳዩት ደግሞ ሀለቃ ሰቋር አባይ የተባሉ የ85 ዓመት አዛውንት የአክሱም ነዋሪ ናቸው።
ዓለምሰገድ ሲቀጥል፣ “የጥላቻቸውን መጠን የሚያሳየው ደግሞ በአማራ ሀኪሞች ይታከሙ እንደሆነ ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ ነው። ከሁለት ሰዎች በስተቀር ሁሉም ኤርትራውያን በአማራ ሀኪሞች መታከም እንደማይፈሩ ሲገልጹ 64.3% የትግራይ ተወላጆች ግን የአማራ ሐኪሞችን እንደማያምኑ ገልጸዋል። ኤርትራ ውስጥ አንድ የ74 ዓመት አዛውንት የሰጡት አስተያየት የሁሉንም የሚወክል ነው። በዓለም ላይ ሁሉም ሐኪሞች ቃለ-መሐላ ይፈጽማሉ፤ ስለሆነም የአማራ ሐኪሞችም ሙያዊ ሥነ-ምግባር እንደሚኖራቸው እጠብቃለሁ፡፡’ ነበር ያሉት፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች የአማራ ሐኪሞችን አያምኑም። ከላይ የጠቀስናቸው ሀለቃ ሰቋር ሲናገሩ፣ ‘የለም፤ አላምናቸውም፤… የአማራ ሐኪሞች በርካታ የተማሩ ትግሬዎችን እንደጨረሱ ሰምቻለሁ። በፈረንጅ ሐኪም ብታከም እመርጣለሁ፡፡ አማራዎች ርኩስ መንፈስ የተጣባቸው ናቸው፡፡ ፈሪዎች ናቸው፤ ለመጥፎ ድርጊት ግን ተወዳዳሪ የላቸውም፡፡ … ለጭካኔያቸው ፈጣሪ ይቅጣቸው።’ … ትግሬዎች የሚያስቡት እያንዳንዱ አማራ የጥፋት ተባባሪ እንደሆነና ሐኪምም ቢሆን አማራ እስከሆነ ድረስ እንደማያምኑት ነው፡፡ አማራ ሐኪሞች ባሉበት ሆስፒታል ትግሬዎች ገብተው በህይወት እንደማይመለሱ ይሰማቸዋል። የ52 ዓመቱ የአክሱም ነዋሪ ሀለቃ ገ/ሕይወት ወልደአብእዝጊ እንዲህ ይላሉ፣ ‘አማራ ሐኪም በፍጹም አላምንም፡፡ የአማራ ሐኪም እንዲነካኝ አልፈልግም፡፡ በደርግ ጊዜ ሆነ ብለው በሽተኞችን ይገድሉ ነበር፡፡ ትግሬዎችን የሚታገሉበት አንዱ መንገድ ይህ ነበር፡፡ ብቃት የሌላቸው የሩሲያ ሐኪሞች እንደሆኑ በሽተኞችን እየገደሉ ያሉት ይለፍፉ ነበር፡፡ ሐቁ ግን አማራ ሐኪሞች ራሳቸው እየገደሉ ነበር በሩሲያ ሐኪሞች የሚያሳብቡት’፡፡”(ሰረዝ የተጨመረ)
በሌላ በኩል የትግራይ ልሂቃንና የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ከአማራ ጋር ጋብቻ መፈጸም እንደማይፈልጉ የገለጹ ሲሆን ከጥላቻቸው አንጻር የሚጠበቅ ነው፤ ካለ በኋላ የአማራ ሐኪሞችን በተመለከተ ከግማሽ በላይ የሆኑት ከፍተኛ አመራሮች የአማራ ሀኪሞችን እንደሚጠራጠሩ በግልጽ ሲናገሩ ሌሎቹ ግን አንፈራም ቢሉም በሌላ በኩል ‘የአማራ ሐኪም ቢያክመን አንፈራም ብንልም በተጨባጭ ግን የምንሄደው ሐኪሞች ተጣርተው ወደሚገቡበት ወታደራዊ ሆስፒታሎች ነው’ ብለዋል።
እዚህ ላይ ህወሓት እንዳደረገው በፕሮግራም ተቀርጾ ይፋዊ ሰነድ ባይሆንም በዕድሜ አንጋፋ የሆኑት የትግራይ ተወላጆች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከህወሓት ዕድሜ በላይ ሥር የሰደደ እንደሆነ መረዳት ተገቢ ነው። ለዚህም ታሪካዊ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል።
ፋሽስቱ የጣሊያን መንግስት ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ለማድረግ የነበረው ህልም በአድዋው አንፀባራቂ ድል ከመከነበት በኋላ ቂሙን ለአርባ ዓመት ይዞ ቆይቶ ዳግመኛ ኢትዮጵያን በ1928 ዓ.ም. ወረረ። በዚህ ወቅት ነጻነቱን ሳያስደፍር የኖረው ጀግናው የኢትዮጵያ ህዝብ ትናንት ድል ከነሳው ጠላት ጋር ገጥሞ ዳግም ድል ሊቀዳጅ ወደሰሜን ዘመተ። ከድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች በወኔ ተንቀሳቀሱ – እንደአድዋው ሁሉ የጠላትን አንገት በጎራዴ እየቀሉ ጥለው ሊወድቁ። ከጫፍ እስከጫፍ በእግርና በፈረስ እየተጓዘ፣ ልጆቹንና ንብረቱን ጥሎ ለሀገሩ ድንበር መከበር ከስድስት ወር በላይ ተጉዞ ወደፍልሚያው ሜዳ የደረሰው የኢትዮጵያ አርበኛ ትግራይ ላይ የገጠመውን ፈተና በተመለከተ ከውጊያው መጀመሪያ እስከመጨረሻ የነበሩ ሁለት የውጭ ሀገር ዜጎች የጻፏቸውና ወደ አማርኛ የተተረጎሙ ሁለት መጻሕፍት – የሃበሻ ጀብዱ እና ቀይ አንበሳ- ማንበብ ጠቃሚ ይሆናል። በአስረጂነት ከ‘የሃበሻ ጀብዱ’ ጥቂት እንጥቀስ።
ጣሊያኖች የአርባ ዓመት ቂማቸውን አድዋን እንደ አዙሪት እየዞሩ እንደ ሐምሌ ዝናብ የቦንብ ናዳቸውን አወረዱባት። የራስ ሥዩም ጦር ፈጽሞ ለጦርነት ዝግጁ አልነበረም። እንዲህ ጣሊያኖች አድዋን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት በቦንብ ሲያጋዩ የራስ ሥዩም ብቸኛ የጦር አበጋዝ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ያልሰለጠኑ ወታደሮቹ ጋር ቆሞ የኮቴ ቀረጥ ይቀበል ነበር። … ራስ ሥዩም ከነጦራቸው ከአድዋ ራቅ ብሎ በየጫካውና በየጥሻው እንደአደፈጡ የንጉሡን መመሪያና ከመሐል ሀገር የሚመጣውን ጦር ተስፋ እያደረጉ ሲጠብቁ፣ … የጣሊያን ጦር አዲግራት ያለብዙ ችግር ገባ። (ገጽ 64)
ቀጥሎም አሁንም ከድንበር ጠባቂው የራስ ሥዩም ወታደሮች ጋር ለሁለት ሰዓት ያህል ተኩስ የገጠመው የሁለተኛው ክፍለ ጦር በጄኔራል ማራቪን እየተመራ አድዋን በእጃቸው … አስገቡ። ጣሊያኖች አድዋን በቀላሉ እጃቸው ያስገቡበት ምክንያት ቀላል ነበር። ዋናው የኢትዮጵያ ጦር ያለው ገና መሐል ሀገር ነው።
የመቀሌ ከተማም አወዳደቅ እጅጉን አስቂኝና አስለቃሽ ድራማ ነበር። የመቀሌው ገዥ ደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሣ ከነጦሩ ወገኑን ከድቶ ለጣሊያኖች በመገበሩ በመቀሌ ከተማ የነበረ ሰው ቢኖር የድሮው የአዲስ አበባ ከንቲባ ባላምበራስ ወዳጆ እና ታማኝ አማካሪያቸው ሻለቃ ካሣ ብቻ ነበሩ። (ገጽ 65)
… ይኼ ደጃዝማች (ኃ/ሥላሴ ጉግሣ) ጦርነቱ ከመጀመሩ ጥቂት ወራት በፊት ጀምሮ ከጣሊያኖች ጋር ሲደራደር ነበር። ልክ ጦርነቱ ሲጀመርና የነጄኔራል ሳንቲኒ ጦር አዲግራት ሲገባ ይኼ ወጣት ደጃዝማች መቀሌን ለቅቆ ከጥቂት ወታደሮቹና አሽከሮቹ ጋር አዲግራት ሸሽቶ ገባ።( ገጽ 67)
ባለቀይ ጺሙ አባቱ ራስ ጉግሣ ከልክ ባለፈ ሁኔታ ከጣሊያኖች ጋር ወዳጅ ነበር። ከጣሊያኖችም በርካታ ትልልቅ ስጦታዎችን ያለምንም ይሉኝታ ይቀበል ነበር። እናም ወጣቱ ደጃዝማች የአባቱን ፈለግ ተከትሎ ሲጓዝ ከርሞ አሁን ከማይመለስበት ክህደት ውስጥ ገባ። (68)
… ሞሶሎኒም ጊዜ ሳያጠፋ ደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሣን ራስ ኃይለ ሥላሴ ጉግሣ ብሎ በጣሊያኖች እጅ በወደቁ የኢትዮጵያ ግዛቶች ላይ በሙሉ ገዥ አድርጎ ሾመው። (69)
… ደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሣ የመቀሌን ቤተመንግስት ሲጣደፍ ጥሎ ሲሸሽ ከተገኙና በጥብቅ ምሥጢር ተይዘው የነበሩት መረጃዎች (ዶክመንቶች) በወቅቱ የኤርትራ ገዥ በነበረው በጄኔራል (በኋላ ማርሻል) ኢሚሊዮ ዴ ቦኖ የተፈረሙ ነበሩ። ከእነዚህ ዶክመንቶች ውስጥ በአንዱ ደብዳቤ ማርሻል ኢሚሊዮ ዴ ቦኖ ለደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ሲጽፍ፣ “የጣሊያን መንግስት በጣሊያን ባንክ ባለው የደጃዝማቹ የግል የባንክ ቁጥር 15000 የምኒልክ ጠገራ የብር ሽልንጎች አስገብቷል” ሲል ጽፏል።(70)
… ደጃዝማች አስፋው ‘ታያለህ እነዚህን አረመኔ ራያዎች? ይኼው ሣምንታቸው ቂጥ ቂጣችንን ሲከተሉን፡፡ እኒህ አረመኔ ራያዎች ብዙ ናቸው፡፡ ጣሊያኖችም መሣሪያና ጥይቶች ስለላኩላቸው አጉል ሰዓት ጠብቀው ሊወጉን ነውና ልጄ በጊዜ ተዋናው ጦር ተቀላቀል’ አሉኝ፡፡ (ደጃዝማች አስፋው በአድዋ ጦርነት ጊዜ አንድ ዓይናቸውን ያጡ፣ በዚህ ጦርነትም በሽምግልና ጊዜያቸው ሊዋጉ የመጡ ጀግና ናቸው) (ገጽ 107)፡፡
… የቀሩት (የምሥራቅ ትግራይ ሰዎች) ከቀበሌያቸው ሳይወጡ ወይ ቀማኛ ሽፍታ ሆኑ አሊያም ለከዳው ለደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሣ ገብረው የዘገየውንና በጉዞ ላይ ደክሞ ወደኋላ የቀረውን የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ይዘርፋሉ፤ ይገድላሉ፡፡ (ገጽ 120-121)
… አቶ ኪሩቤል ‘ዋይ ዋይ ዋይ ዋይ ትናንትና ብዙ ሰው ገደሉ፤’ አለኝ፡፡ ‘ማን ገደላቸው’ ስል ጠየቅኩት፡፡ ‘ዋይ ዋይ የትግራይ ሽፍቶች ናቸዋ’ አለኝ አስተማሪው ኪሩቤል፡፡ ለምን የገዛ ወንድሞቻቸውን ይገድላሉ ሊሆን አይችልም! ስል ሁኔታው ሊገባኝ ባለመቻሉ ከአቶ ኪሩቤል ጋር ሙግት ውስጥ ገባሁ፡፡ ከመሀል ሀገር ስድስትና ሰባት ወር ሙሉ ፍዳውን እያየ ሲጓዝ ከርሞ እዚህ የደረሰው ወንድማቸው፣ የእነዚህን ምስኪኖች ህይወትና ንብረት ከጠላት ለመከላከል የገዛ ህይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ፣ ቤት ንብረቱን በትኖ መከራውን ባየ ለምን ይገድሉታል? ስል በድጋሜ አቶ ኪሩቤልን ጠየኩት፡፡ አብዛኞቹ የትግራይ ሰዎች ይህንን የተቀደሰ ሃሳብ ይቃወሙታል አለኝ፡፡ (ገጽ 121)
… የትግራይ ሽፍቶች በጦራችን ላይ ተኩስ ከፍተው ብዙ ወታደሮቻችንን ከመግደላቸውም በላይ አምስት ሣጥን ሙሉ ጥይት የጫኑ አጋሰሶቻችንም ዘረፉን፡፡ (ገጽ 122)
… ከጣሊያን ጦር ጋር ተቀላቅለው የሚዋጉ የኤርትራ ተወላጆች በቡድን በቡድን እየሆኑ እየከዱ ከመምጣታቸውም ሌላ በውጊያ ጊዜ በኢትዮጵያውያን ላይ ምንም ሳይተኩሱ ወይም ወደሰማይ እየተኮሱ ከኢትዮጵያውያን ጋር ይቀላቀሉ ነበር (ገጽ 138)፡፡ አለቆቻቸውን እየረሸኑም ይመጡ ነበር፡፡ በሚከዱት ላይ የጣሊያን መንግስት ጠበቅ ያለ እርምጃ በቤተሰባቸው ላይ ይወስድ ነበር።
… አይቦታ ጦር ሰፈር ገና ድንኳኖቻቸውን ያልነቀሉ ወታደሮቻችን ከትግራይ ሽፍቶች ጋር የሞት ሽረት ትግል ያካሂዱ ነበር። (ገጽ 146)
… ከራስ ካሣ የጦር ሰፈር በሩጫ ከአራት ቀን በኋላ ከራስ እምሩ ዘንድ የሚደርሰውን መልዕክተኛ ሯጭ የትግራይ ሽፍቶች እየገደሉ መልዕክቷን በይሁዳ ሽልንጎች ለጣሊያኖች መሸጥ ጀምረዋል። ጣሊያኖች በሚያጎርሷቸው ጉርሻ ልባቸው ያበጠ ሽፍቶች ለወታደሮቻችን የሚመጣውን ማንኛውንም ነገር መንገድ እየጠበቁ ይዘርፋሉ።(ገጽ 157)
… ስንጓዝ ቆይተን ካንዲት ትንሽ መንደር ደረስንና የሚበላ ነገር፣ ቢያንስ አንባሻ ብንገዛ ብለን ወደመንደሯ አመራን። ብዙም ወደመንደሯ ሳንዘልቅ መንደርተኞቹ ከቤታቸው ጣሪያ ላይ ሆነው የመሣሪያቸውን አፈሙዝ በእኛ ላይ ደቅነው እያፈራሩ ጮሁብን። ሁሌም ከእኛ የማይለየው ጓደኛችን ልጅ ወልደገብርኤል እንደተረጎመልን መንደርተኞቹ ወደመንደሯ ከዘለቅን እንደሚተኩሱብንና ወደመንደሯዘልቀን እንዳንገባ እንደሚያፈራሩን ነገረን። ልጅ ወልደገብርኤል መንደርተኞቹን ቢያንስ አንባሻ እንዲሸጡልን ሊያግባባቸው ቢሞክርም አሻፈረኝ ስላሉ እንደራበን በጉዟችን ቀጥለን ማምሻው ላይ ጊባ ወንዝ ደረስን።(ገጽ 161)
… እነ አቢቹን አንድ ሌሊት ከትግራይ ሽፍቶች ጋር ችግር ገጠማቸው። የትግራይ ሽፍቶች አንድ አስቸጋሪ መንገድ ላይ አግኝተውት አናሳልፍም በማለት በከፈቱት ተኩስ ሽፍቶቹ የአቢቹን ሁለት ተዋጊዎች ይገድላሉ። (አንባቢዎቼ አቢቹ ወይም ልጁ የ17 ዓመት ወጣት፣ ጣሊያኖችንም ሆነ የትግራይ ባንዳዎችን ቁም ስቅል ሲያሳይ የነበረ፣ ሁለት ወንድሞቹን የገደለውን የጣሊያን ጦር አይቀጡ ቅጣት የቀጣ፣ ንጉሡ ሳይቀሩ በጀግንነቱ ተገርመው በሌለበትና ይፋዊ ባልሆነ ሁኔታ ደጃዝማች ብለው የጠሩት ልበ-ሙሉ የኦሮሞ ልጅ ነው!) አቢቹ ችግሩ እንደተፈጠረ ከሽፍቶቹ ጋር ተደራድሮ ለማለፍ ቢሞክርም ሽፍቶቹ አንዲት መንደር ውስጥ መሽገው ተኩስ ሲከፍቱበት፣ አቢቹ ትዕግስቱ አልቆ ሽማግሌዎችና፣ ሴቶችና ህፃናት መንደሯን ለቀው እንዲወጡ ካደረገ በኋላ መንደሯን በእሳት አጋየው። ከየመሸገበት እየወጣ ሽሽት የጀመረውን ሽፍታ እያሳደደ ቀጠቀጠው። ጥዋት የተገኘው የመንደሯ አመድና እዚም እዚያም የወደቁ የሽፍታ ሬሣዎች ነበሩ። (ገጽ 189-190)
… በጨለማ ስንጓዝ ከሩቅ የውሾች ጩኸት ሰማን። የውሻ ጩኸት ጥሩ ምልክት ነው። ርሃቡም እየጠነከረብን ስለነበር ቢያንስ የሆነ የሚበላ ነገር መግዛት እንኳን ብንችል ብለን አቅጣጫችንን የውሾችን ጩኸት ወደምንሰማበት አደረግን። ብዙም ሳንጓዝ ከአንዲት መንደር ደረስን። የደቡክ መንደር ነበረች። ወደ ደቡክ ቀበሌ ብዙም ሳንጠጋ አንዱን ወታደር ወደቀበሌዋ ሄዶ ቢቻል አንባሻና የሚጠጣ ነገር አለበለዚያም ዶሮና ጥራጥሬ ገዝቶ እንዲመጣ ላክነው። ወታደሩ ሲጠጋ ውሾች ጮኹ። ‘ማነው’ ሲሉ በአማርኛ ‘አንባሻ ወይም ዶሮ ለመግዛት ነው’ ብሎ ሲያናግራቸው ደጋግመው ተኮሱበት። እነዚህ ምስኪን ወታደሮች ቤት ንብረታቸወን በትነው፣ የእነዚህን መንደርተኞችና መሰሎቻቸውን ንብረትና ደህንነት ከጠላት ለመካለከል እዚህ ድረስ መጥተው፣ እነዚህ ውለታ-ቢስ መንደርተኞች ግን ተቀብሎ በማስተናገድ ፋንታ የጥይት ሰላምታ ያቀርቡላቸዋል፤ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ይተኩሱባቸዋል። ወልደገብርኤል በትግርኛ አናገራቸው፤ እንዲጠጋ ፈቀዱለት። ‘ለምን በእኛ ወታደር ላይ ተኮሳችሁ’ ሲባሉ ‘መተኮስማ አለብን። ታዘናል።’ ነበር መልሳቸው። ‘
‘ማን አዘዛችሁ’
‘ጣሊያኖች!’
የታዘዙበትን ወረቀት አምጥተው አሳዩ። ወረቀቱ እንዲህ ይላል፤
ለትግራይ ህዝብ
በሀገራችሁ ሰላም አስፍነን ስልጣኔና ብልፅግናን እንድናሰፍን እግዚአብሔር ልኮናል። ይሁን እንጂ የአማራና የኦሮሞ ጨቋኞች፣ ቀማኛና ሰው በላ ወታደሮቻቸውን አሰልፈውብን ይኼንን የተቀደሰና ከእግዚአብሔር የተሰጠንን ተልዕኮ እንዳንፈጽም እያወኩን ነው።
የተከበርክ የትግራይ ህዝብ ሆይ፣ እነዚህን የአማራና የኦሮሞ ቀማኛ ሽፍቶች በመንደርህ ሲዘዋወሩ ብታገኝ እህል ውኃ ሳታቀምስ፣ ጥይትህን እየተኮስክ እንደውሻ ከመንደርህ እንድታባርራቸው እናሳስብሃለን።
እነዚህ የአማራ ሽፍቶች ወደመንደራችሁ ተጠግተው የሚበላ ሆነ የሚጠጣ ነገር፣ ምንም ዓይነት እርዳታ እንዳታደርጉላቸው አጥብቀን እናሳስባለን። ከመሃላችሁ ይኼን ትዕዛዛችንን ተላልፎ አንድ ሰው እንኳን ለአማራ የሽፍታ ወታደር አንዲት አንባሻ ሲለግስ ወይም ሲሸጥ ቢገኝ ምህረት የሌለው ቅጣታችን በሁላችሁም ላይ ይደርሳል።
በመሃላችሁ የራሳችን ሰዎች ስላሉን ጨለማን ተገን አድርጋችሁ ትዕዛዛችንን ተላልፋችሁ ብትገኙ ጉህ ሲቀድ አውሮፕላኖቻችን መጥተው መንደራችሁን ዶግ አመድ ያደርጓታል።
ይህን ትዕዛዝ አሜን ብሎ የተቀበለው የትግራይ ህዝብም ትዕዛዙን ማክበር ብቻ ሳይሆን ጣሊያኖች ገና ባልደረሱበት ቦታ ሁሉ በየቤቱ የጣሊያንን ባንዲራ ያውለበልባል።(ገጽ 214)
… በጠባብና በገላጣ መንገድ ስንጓዝ ከቁጥቋጦ ውስጥ የታጠቁ የትግሬ ባላገሮች ወጡና ወደእኛ መጡ። ሁሉም የታጠቁ ነበሩ። የጠላትነት ስሜት አይታይባቸውም። መሪያቸው አንድ ወጣት ሹም ነው።
‘በሥዩም አምላክ! ወዴት እየሄዳችሁ ነው’ አለ።
‘በካሣ አምላክ! ወደራስ ሙሉጌታ እየሄድን ነው’ ሲል ወልደገብርኤል መለሰ። በራስ ካሣና በራስ ሥዩም የተፈረመ የይለፍ ደብዳቤ አሳየው።
ይኼ ወጣት ሹምና ተከታዮቹ የከዳተኛው፣ የባንዳው የደጃዝማች ኃ/ሥላሴ ጉግሣ ተከታዮችና አገራቸውን ከድተው ከጣያኖች ጋር አብረው የገዛ ወንድሞቻቸውን እየወጉ በገዛ አገራቸው ላይ የዘመቱ ሆዳሞች፣ ወራዶች ናቸው ሚል ጥርጣሬ የነበረው አንድም ሰው አልነበረም። የደጃዝማች ኃ/ሥላሲ ጉግሣ ወታደሮች እንደጣሊያኖች መለዮ አይለብሱም። ሰላማዊ ሰው፣ የራስ ሥዩም ወታደር ወይም ሌላ መስለው ያታልላሉ።
ወጣቱ መሪ ደብዳቤው ትክክል እንዳልሆነ ገልጾ፣ ‘አንተና ፈረንጁ መሄድ ትችላላችሁ። የቀሩት ሃምሳዎቹ ታጣቂ ወታደሮች ግን ትጥቃቸውን ፈትተው ከእኔ ጋር መሄድ አለባቸው’ አለው። ከልጅ ወልደገብርኤል ጋር ከፍተኛ ክርክር ፈጠሩ (ጨዋታው በትግርኛ ነው)። እሱን አስቀርተው ሌሎቹን አንድ በአንድ በጥይት ለቅሞ ለመጨረስ ነበር። … በሰላም ይሄዱ የነበሩ ወታደሮች ለጥቂት ጊዜ ራስ ቅላቸውን ያዝ ደርጉና ወደመሬት ዝልፍልፍ ብለው ይወርዳሉ፣ ይወድቃሉ። ከየአቅጣጫው ከየቁጥቋጦው ስር ትንሽ ጉም መሳይ ብን እያለች ስትወጣ ጠላት የመሸገበትን ቦታ ስለምታጋልጥ ወታደሮቻችን ጭሷን ትከትለው ሽፍታውን በመሸገበት ያተኙትና እንደሁልጊዜው ሁሉ ‘የት አባቱ! ደሞ ለሽፍታ!’ ይላሉ።
… የራስ ሙሉጌታ ወታደሮች የጣሊያን አውሮፕላኖች እንደዶፍ ከሚያወርዷቸው ቦንቦችና የጢስ ሞርዞች ለማምለጥ በቻሉት ፍጥነት በየጫካውና በየጢሻው እየገቡ ሲበተኑ፣ ቀድሞ መሽጎ ይጠብቃቸው የነበረው የራያና አዘቦ አረመኔ ሽፍታ በጣሊያን መሣሪያ እያለመ ለቀማቸው። ገና ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ጣሊያኖች በወኪሎቻቸው አማካኝነት ሰርጎ ገቦችን እየላኩ የራያና አዘቦን ሰዎች ገንዘብ እየሰጡና ዘመናዊ መሣሪያ እያታጠቁ በገዛ ወንድሞቻቸው ላይ እንዲዘምቱ አደረጓቸው። እነዚህ የራያና አዘቦ ከሃዲ ሽፍቶች ጦርነቱ ከተጀመረ ሰሞን ጀምሮ ከመሀል አገር ተነስቶ ወደጦር ሜዳ የሚገሰግሰውን የኢትዮጵያ ጦር አሳቻ ቦታ እየጠበቁ ዘረፉት፣ ገደሉት። እነሆ ዛሬ ከስድስት ወር በላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ፍዳውን ሲያይ ኖሮ፣ በትናንቱ ጦርነት ተሸንፎ በመሸሽ ላይ ያለውንና ነፍሱ እስክትወጣ የደከመውን የራስ ሙሉጌታ ሠራዊት እንዲህ ተበትኖ አገኙት፡፡ በጥይት ኢላማቸው ያልገባላቸውን፣ ደክሞት በየዛፉ ጥላ ስር ያረፈውን፣ በእንቅልፍ እጦት ሲሰቃይ ሰንብቶ ለአፍታ ጋደም ያለውን ሠራዊት ድምጻቸውን አጥፈፍተው እየተጠጉ በጩቤ ከኋላው እየወጉ ገድለው የመጨረሻ ንብረቱን ዘረፉት፡፡(ገጽ 245)
… እዚህም እዚያም ወታደሮቻችን ሳይተኩሱ ወደመሬት መውደቅ ጀመሩ፡፡ ወዲያው በማናየው ጠላታችን ላይ የመልስ ተኩስ ከፈትን፡፡ መሽጎ ተኩስ የከፈተብን ጠላታችን ከጥቅት ደቂቃዎች ውጊያ በኋላ ፀጥ አለ፡፡ አዎ የትግራይ ሽፍቶች ነበሩ፡፡(ገጽ 271-272)
… የሦስቱ ራሶች ጦር እንደገና በሦስት ረድፍ ተሰልፎ ለሦስተኛ ጊዜ ማይጨውን ለመያዝ ወደፊት ሄደ፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ የተደረገው ይኼው ማይጨውን የመያዝ ጦርነት ዕድሜ ለአራተኛው ረድፈኛ ጦረኞች የጣሊያኑን ሠራዊት ወገቡ ላይ ሰብረው የሚገባበት ሲያሳጡት፣ የሦስቱ ራሶች ጦር የታሊያኑን ዋና ምሽግ ሰብሮ ገባ፡፡ ድል በኢትዮጵያውያን እጅ የገባች መሰላች፡፡ በዚች ቅጽበት ዳግም አድዋ ሊደገም የሰዓታት ልዩነት ሲቀረው እነዚህ ከሃዲዎች ራያዎችና አዘቦዎች ድልን በእጁ ሊያስገባ የተቃረበውን የገዛ ወንድማቸውን ከጀርባው ገብተው ጨፈጨፉት፡፡ ድልን በእጁ ሊጨብጥ ወደፊት የገሰገሰውን የእናታቸውን ልጅ ድል ነሱት፡፡ አዎ እነዚህ ከሃዲዎች ጦርነቱን ወስነዋል፡፡ ታሪክም ሰርተዋል፡፡ ታሪኩ ግን የክህደት ታሪክ ነው፡፡ ለሰላሣ ሽልንግና ለአዲስ የጣሊያን መሣሪያ ሲሉ ለጣሊያን ባንዳነት አድረው የገዛ ወንድማቸውን ክደውታል፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ዕድል ተወስኗል፡፡ ተሸንፈናል፡፡ ኢትዮጵያውያን በማይጨው ጦርነት ተሸነፉና በያቅጣጫው ወደየትውልድ መንደራቸው መሸሽ ጀመሩ፡፡(ገጽ 293-294)
… ምርጥ ምርጦቹ የኢትዮጵያ ልጆች በተንቤን፣ በማይጨው፣ በአሸንጌ ሐይቅ ዙሪያ ወድቀው የአሞራ እራት ሆነዋል፡፡ ከዚህ የተረፉትን ሽፍቶች፣ ራያዎችና አዘቦዎች አጉልና አሳቻ ቦታ እየጠበቁ ለዘለዓለሙ አስቀርተዋቸዋል፡፡(ገጽ 320)
*******
ህወሓት የጀግንነት ታሪካችን የሚለን ይህንኑ ነው፡፡ ዓለምሰገድ አባይ በጻፈው መጽሐፍ እንደጠቀሰው ለትግራዮች ጠላት አማራ እንጂ ጣሊያን ወይም ቱርክ አሊያም ግብጽ አይደለም በማለት የገለፀው በተግባር የተረጋገጠበት ታሪካዊ ክስተት ነበር፡፡ ህወሓትም ይህንን የአባቶቹን ውርስ ይዞ ነው የተነሳው፡፡ በኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ በማድረግ ዴሞክራሲ፣ ሰላምና ልማት ማረጋገጥ ሳይሆን አማራን ማጥፋት ዋና ዓላማው ያደረገውም ለዚህ ነው፡፡ ለዚህ ተግባሩም በትግሬዎች ቁንጮነት የሚመራው ብአዴን የህወሓት ቀኝ እጅ ሆኖ ተመሠረተ፡፡ መለስ፣ አቦይ ሰብሃት፣ አባይ ፀሐዬና የመሳሰሉት ጠፍጥፈው የሰሩት ብአዴን (ኢህዴን) ሲጀመርም በርካታ ሐቀኛ አማራዎችን በልቶ ነው የተመሠረተው፡፡ የኢህዴን ቅድመ ዘግጅት ሲደረግ መለስ አንድ ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣል፡፡ ይህም የትግራይ ህዝብ ደመኛ ጠላት የአማራ ብሄር መሆኑን እንዲቀበሉ ነበር፡፡ በርካታ ታጋዮች ይህንን መቀበል አልተቻላቸውም፡፡ አንድን ህዝብ እንደህዝብ ጠላት ብሎ መፈረጅ ታሪካዊ ስህተት ከመሆኑም ሌላ ሀገሪቱን አደጋ ውስጥ የሚጥልና አለመረጋጋት የሚያሰፍን ነው ሲሉ ሞግተው የህወሓትን አቋም እንደማይቀበሉ ገለጹ፡፡ መሰሪው መለስ የሚቀበሉትንና በአቋማቸው ፀንተው የአማራ ህዝብ ጠላት ነው ብለን አንፈርጅም ያሉትን ለየ፡፡ እነዚህ አፈንጋጮች ተብለው ጉድጓድ ተምሶላቸው በሌሊት በጥይት ተደብድበው በረሃ ቀሩ፡፡ የመለስን ቡራኬ የተቀበሉት የትግራይ ዘር ያላቸው የኢህዴን አመራሮች ከመለስ ቀጭን ትዕዛዝ እየተቀበሉ ቀጠሉ፣ ለምዳቸውን ቀይረውም የአማራ ህዝብ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው ተሾሙ፡፡ ዛሬም እየገደሉት፣ እያስገደሉት፣ እየሰደቡት፣ እያሰደቡት ከአማራ ህዝብ ትከሻ ላይ ፊጥ እንዳሉ ናቸው፡፡
ህወሓት አሁንም ፀረ-አማራ ሥራውን አጠናክሮ እንደቀጠለ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ብሔር ሌት ተቀን አማራ ጠላትህ ነው፣ አማራ በአካባቢህ ካለ አስወግደው፣ አማራ አረመኔ ነው እያለ ይለፍፋል፣ ያስለፍፋል፡፡ በየክልሉ ያሉ አሻንጉሊት ሹማምንት ለህዝባቸው የአማራን ጠላትነት፣ ራሱን ቀና እንዳያደርግ መቀጥቀጥ እንዳለበት፣ ሞራሉ መሰበር እንዳለበት፣ ዕረፍት ማግኘት እንደሌለበት እንዲያሰተምሩ ይሰብካቸዋል፡፡ አንድ ተጨባጭ ማስረጃ እናንሳ፡፡
የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት የሆነው አብዲ መሐመድ ዑመር የጎሣ መሪዎችን ሰብስቦ የሚከተለውን ምክር ሲሰጥ ምስልና ድምፁን ዓለም ሰምቶታል፤
“ዛሬ ትግሬዎች ከማንም በላይ ሶማሌዎችን (ኦጋዴኖችን) ይወዳሉ፡፡ ነገር ግን ኦጋዴኖች ናቸው ተኩስ ከፍተው የሚገድሏቸው፡፡ ትግሬ ከማንም በላይ ኦጋዴንን ይወዳል፤ እናም ኦጋዴንን አስታጥቆ አገሪቱን ከእኛ ጋር ሆኖ የመምራት ሀሳብ ነበረው፡፡ ትግሬ የሚፈልገው አማራ ተመልሶ ወደሥልጣን እንዳይመጣ ነው፡፡ ስለዚህ ኦጋዴንን ከጎኑ በማድረግ አማራው ተመልሶ ሥልጣን እንዳይዝ የማድረግ ዓላማ ነበረው፡፡ እኛ ደግሞ በትግሬዎች ተኩስ ከፈትንባቸው፡፡ ዋናው ችግር ኦጋዴኖች ጉራጌውንም፣ ኦሮሞውንም ትግሬውንም ሁሉንም አንድ ላይ ነው አማራ እያሉ የሚጠሩት፡፡ እነሱ እኮ እርስ በርስ የማይታረቁ ሰዎች ናቸው፡፡ እኛ ግን እነዚህን ሰዎች አንድ ላይ ጠቅልለን አማራ እንላቸዋለን፡፡ ለምሣሌ፡- አማራ እና ትግሬን አንድ ላይ ጨፍልቀን አማራ እንላቸዋለን፡፡ ደግሞ አማራና ኦሮሞን እንደዚሁ አንድ ላይ ጨፍልቀን አማራ እንላቸዋለን፡፡ እነሱ እኮ መቸውንም ሊታረቁ የማይችሉ ናቸው፡፡ እነዚህን አብረው አንድ ላይ ሆነው መሄድ የማይችሉትን ሰዎች አንድ ላይ እየጨፈለቅን አማራ ስለምንላቸው በዚህ ምክንያት ለማደግ አልቻልንም፡፡ ኋላቀር ሆነናል፡፡”
በፕሬዚዳንቱ ንግግር መሐል አንድ ሽማግሌ ጠየቁ፡- “እኛ እነሱን ነጣጥለን የምናያቸው ከሆነ እነሱስ በእኛ ላይ ተባብረው አያጠቁንም?”
ፕሬዚዳንቱ መለሰ፣ “እነሱ መቼም መቼም ቢሆንም ተባብረው አንድ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ አንድ ሶማሌ አዲስ አበባ ሲሄድ ትግሬ ስር ነው የሚገባው፤ ምክንቱም ትግሬዎች ናቸው ለእሱ የሚቀርቡት፡፡”
ልብ በሉ! አማራና ትግሬ አንድ ሊሆኑ የማይችሉ ባላንጣዎች መሆናቸው ለፕሬዚዳንቱ በሚገባ ተነግሮታል፤ እሱም ወደህዝብ እያወረደው ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የአማራ ተወላጆች ከሥራ እንዲፈናቀሉ፣ ከጽዳትና ተላላኪ ከፍ ያለ ሥራ ላይ እንዳይመደቡ ትዕዛዝም አስተላልፎ እየተተገበረ ነው፡፡ ለፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ የሚሰጠው ሐረር ያለው ጄኔራል አበራ መሆኑን እንዳትረሱ፡፡ ፕሬዚዳንቱም ጄኔራሉን ሳያስፈቅድ አንዲት ትንሽ ውሳኔ አይወስንም፡፡
ለማጠቃለል፣ በአማራ ህዝብ ላይ የማያባራ ዘመቻ ከተከፈተ የቆየ ቢሆንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ስለዚህ የአማራ ህዝብ ምን ያድርግ? ለየቱ ግብ ይታገል? ለመገንጠል? ለተሟላ የራስ አስተዳደር? አማራ ራሱን ችሎስ መደራጀት ይኖርበታል ወይስ የለበትም?
እመለሳለሁ። ቸር ቆዩኝ!