Bete Amhara

Bete Amhara

Monday, June 15, 2015

የቤተ አማራ ጥቅም ሳይከበር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ሊከበር አይችልም!
አንድ የኮካዎች መድረክ ላይ ነው ፤ አብዛኛው ተሳታፊዎች ተጋሩ ናቸው። ክርክሩ ደግሞ በዋነኝነት ስለ ትግራዩ አረና ፓርቲ ሲሆን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ህዋሃትን በተመለከተ። አረና ፓርቲ ማለት እንደ እነ አብርሃ ደስታ አይነት እንቁ ወጣት ፖለቲከኞችን እና አንጋፋውን አቶ አሰገዶም ገብረ ስላሴን ያቀፈ ሲሆን ህዋሃት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በትግራይ ክልል የተቋቋመ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ፓርቲው አዲስ እንደመሆኑ መጠን የራሱ የሆነ ተቋማዊ ድክመቶች እንደሚኖሩበት መገመት ቢቻልም ባለው አስቸጋሪ ሁኔታ እንደ አንድ ፋና ወጊ የፖለቲካ ፓርቲ ግን ለሚያደርገው ትግል ሊበረታታ የሚገባው ተቋም ነው። በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያዊ አቋሙ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም።
ከክርክሩ እንደተረዳሁት ከሆነ ይህ ኢትዮጵያዊ አቋሙ በተለይም ደግሞ ከሌሎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር የሚያደርገው ግንኙነት በህዋሃት ኮካዎች ዘንድ አልተወደደለትም።
አንደኛው ተከራካሪ(በነገራችን ላይ ይህ ኮካ እዚሁ ፌስቡክ መንደር የሚልከሰከስ እጅግ ዘረኛ የሆነ እና 'መለስ ኢየሱስ ነው' ብሎ የሚከራከር አይነት ቅልጥ ያለ ካድሬ ነው፤ስራውን እውቅና ላለመስጠት ስሙን ለጊዜው ትቸዋለሁ) 'አረና ማለት እኮ የደላላዎች ፓርቲ ነው' ሲል ወቀሳውን ያቀርባል። የደላላዎች ፓርቲ ማለቱ ለባለፉት 24 አመታት ተነጥሎ የሚገኘውን የትግራይን ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያ ወንድሙ እና እህቱ ጋ ሊያገናኝ ጥረት ማድረጉን እንደ ክህደት ቆጥሮት እንደሆነ ለመረዳት ነብይ መሆን አያሻም።
በተቃራኒ የቆመ አንድ እውነተኛ ተከራካሪ ግን እንዲህ ሲል መልስ ሰጠው " የአረና ሃጢአት ሃገር ውስጥ ከሚገኙ ፓርቲዎች ውስጥ ትብብር መፈለጉ ነው ? ያንተ ፓርቲ (ህዋሃትን ማለቱ ነው) አይደለም እንዴ የሃገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ለጎረቤት ሃገር አሳልፎ ከመስጠት አልፎ በሃገር ውስጥ ሁሌ ሁከት የሚፈጥረው" ሲል እጅግ የሚያረካ መልስ ሰጠው። አንዳንዴ እንደዚህ አይነት ደፋር እና ግልጽ ጥቂት የትግራይ ወጣቶችን ሳይ ለምን እንደሆነ አላውቅም ውስጤን ደስ የሚል ስሜት ይሰማዋል ። ነገር ግን ይህ የአበደ የህዋሃት ካድሬ እጅ መስጠት አልፈለገምና የሚከተለውን እጅግ የሚያቆስል መልስ ሰጠ።
"ብሄራዊ ጥቅም ምናምን ተወው እና ቢያንስ ፓርቲያችን በትግራይ ጉዳይ ላይ ድርድር አያውቅም። አረና ፓርቲ ግን የትግራይን ጥቅም ለነፍጠኛ ሃይሎች (የፈረደበት አማራ መሆኑ ነው) አሳልፎ ሲሰጥ ብዙ ጊዜ አይቻለሁ" አለ። መቼም የሚያናድድ አባባል ነው። እውን አብርሃ ደስታ ወይንም አቶ አሰገደ ገብረስላሴ ስለ ኢትዮጵያዊነት አጥብቀው ከመጮሃቸው ውጭ መቼ እና የት ይሆን የትግራይን ህዝብ የሚጎዳ ነገር አድርገው ለአማራው ወይንም ለሌላው ህዝብ አሳልፈው የሰጡት? ለካ በሃገሪቱ ስላሉ ብሄሮች ፍትህ፤ ነጻነት እና እኩልነት ማውራት የትግራይን ህዝብ ጥቅም አሳልፎ መስጠት ነው እንደነዚህ ሰዎች አባባል።
እንደዚህ ኮካ እና እንደ ብዙዎች የህዋሃት አመራሮች እና ካድሬዎች አስተሳሰብ ከሆነ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ከተከበረ የትግራይ ጥቅም ይጎዳል፤ መጀመሪያ የትግራይ ጥቅም ሲከበር ብቻ ነው ብሄራዊ ጥቅም ብሎ ነገር ከዚያ በኋላ ሊወራ የሚችለው ማለት ነው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም መቃብር ቢወርድም ህዋሃት የትግራይን ህዝብ ጥቅም እስካስከበረ ድረስ ሺህ አመት እንዲገዛ ነው የእነዚህ ሰዎች ምኞት። በተረፈ በሃገሪቱ ሰላም፤ የብሄር እኩልነት እና ነጻነት ተከበረ ማለት የትግራይ ጥቅም ገደል ገባ ማለት ነው።
እናስ ቤተ አማህራዎች ሆይ እንዴት ብለን ነው ከእነዚህ ሰዎች ጋ ልንኖር የምንችለው? እንዴት ነው በእናንተ መቃብር ላይ የእኛ ጥቅም ይከበር ከሚሉን ሰዎች ጋ አብረን የምንዘልቀው? እንዴት ነው የትግራይ ህዝብን ጥቅም ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም መከበር በላይ ከሚያዩ ሰዎች ጋ ለአንዲት ደቂቃ እንኳ አብረን መዋል የምንችለው? እረ በእውነት ያማል። ማንስ ነው የአማራ ህዝብ ጥቅም ሳይከበር ብሄራዊ ጥቅም ሊኖር አይችልም ብሎ በድፈረት የሚከራከረው ወገን? እኒህን ጥያቄዎችን ቆም ብለን ራሳችንን ስንጠይቅ የቤተ አማራ ምስረታ አስፈላጊነት ፍንትው ብሎ ይታየናል።
እኛ በአንድነት ስም ራሳችንን ስናታልል ሰዎች መቃብራችንን እየቆፈሩ ነው። የጥፋት ውሃ ሁሌም እየተደገሰልን ነው፤ ከተማሰው ጉድጉድ ማምለጥ የምንችለው ደግሞ እኛነታችንን በቅጡ ለይተን በጋራ አይሆንም ማለት ስንችል ነው። የአማራ ህዝብን ጠቢብነት፤ ጀግንነት እና ጽናት ተላብሰን ወደ አንድ መድረክ መምጣት ከቻልን ከቶ ሊያቆመን የሚችል ሃይል አይኖርም። የቤተ አማራ ምስረታ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ የሆነበት ወቅት ላይ እንገኛለን። የአንድነት ሃይሎችም ስራችሁን ስሩ። እናንተ ቀድማችሁ ኢትዮጵያን ነጻ አውጥታቹህ እኛንም ነጻ ካወጣችሁን እሰየው፤ እስከዚያው ግን ስለ አንድነት እያወራን ቆመን የምንጠብቅበት ሰአት የለንም። ሁሉም ራሱን ነጻ ያውጣና ከዚያ በኋላ ስለ አንድነት እና አብሮ መኖር እናዎራለን። ትዳር በመፈቃቀድ እንጅ አንዱ የበላይ አንዱ የበታች ሆኖ በብረት ሰንሰለት የሚኖርበት ተቋም አይደለም እና ዛሬውኑ እንነሳ ፤ጉዟችንን ወደ ተሰፋይቱ ምድር ወደ ቤተ አማራ እናድርግ።
መልካም የሆሳእና በአል ለሁሉም ቤተ አማራዎች!
አክባሪያችሁ ካለሁበት ቤተ-አምሓራ