Bete Amhara

Bete Amhara

Monday, June 15, 2015

የግድ መነበብ ያለበት (ከጦቢያ ቅጣው)
================================
“ተንኮለኛ ምጣድ በጀርባዬ ዞሮ ለካ ጥላት ብቻ ሆኛለሁ ዘንድሮ” አማራዉን ጥርሱን የነከሰበት ወያኔ ብቻ አይደለም፡፡ ወያኔ በአማራዉ ላይ ያለዉን የጅምላ ጥላቻ በብሄር ዙሪያ ለተደራጁ ቡድኖች አድሏቸዉ ጥላቻቸዉን ከበደኖ እስከ ጉራ ፈረዳ እስከ ቤኒሻንጉል አይተናል፡፡ እነዚህ ቡድኖች ስለዛሬ ሲጠየቁ ትላንት አማርኛ ቋንቋ እየተነገረ ሲጨቆኑ እንደነበር በፀፀት የሚናገሩ ናቸዉ፡፡ ወያኔ በአማራዉ ዙሪያ የጣደዉ የጥላቻ ምጣድ አማራዉ ጥላት በጥላት እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ሃይሌ ስለአማራ የተራድኦ እና የዕርቅ ድርጅት ያሉትን እንዲህ ማህበራዊ ድረ-ገፅ ሲንገዋለል አገኘሁትና አነበብኩት፡፡ ሃሳቡ ሲጨመቅ አማራዉ ለራሱ ህልዉናዉና ለሌሎች ቤዛ ይሆን ዘንድ ይደራጅ ይላል፡፡ አማራዉ የአባቶቹን ግዴታ ለመወጣት ታሪኩና ብዙህነቱ ገፊ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መናገራቸዉም የሚያስማማኝ ጉዳይ ነዉ፡፡ ሆኖም ግን የፕሮፌሰሩ ፅሁፍ “የድርጅቱ መቋቋም ኢትዮጵያዉያንን ሁሉ የሚያስደስትና ተስፋ የሚያበስር (የወያኔን ቡድን ብቻ የሚያሰጋ) መሆኑን በግልፅ ቃላት መቅረብ አለበት”በማለት ይናገራል፡፡ “የወያኔን ቡድን ብቻ የሚያሰጋ” የሚለዉን ፍሬ ነገር አጠልጥለን ጉዳዩን እንበልጥጠዉ፡፡ ችግሩ አማራዉ ቢደራጅ ስጋቱ የወያኔ ብቻ አለመሆኑ ነዉ፡፡ አማራዉ እንዲጠላ እና ማስፈራሪያ እንዲሆን መርዙን የረጨዉ ወያኔ ለመሆኑ ነጋሪ አያስፈልግም፡፡ከወያኔ ዉጪ ያሉ ቡድኖችም አማራዉን የሚያዩበት መነፀር ከወያኔ ፋብሪካ የተሰራ በመሆኑ ስጋቱን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ወያኔ የአማራዉ መደራጀት ስጋቱ የእሱ ብቻ እንዳይሆን አድርጎ ፖለቲካዉን ሰርቶታል፡፡ ህወሓት ከአማራዉ የሚመጣዉን ሃይል ብቻዉን ሊቋቋም እንደማይችል ስለሚያዉቀዉ የዉሸት ታሪክ እየፈጠረም ሆነ የይስሙላ ሃዉልት እየሰራ ሌሎች ቡድኖችን በዙሪያዉ ማሰለፍ ችሏል፡፡ እንድ ፕሮፌሰሩ ገለፃ አማራዉ የሚያቋቁመዉ የተራድኦ እና የእርቅ ድርጅት ዋናዉ ዓለማ ዕርቀ ሰላም ማዉረድ ነዉ ይላል፡፡ ዕርቅ በባላጋራ መሃከል የነበረ ጥልን አስማምቶ ማስወገድ ነዉ፡፡ አንድ ሰዉ ሆነ ቡድን በራሱ ጉዳይ ላይ አስታራቂ ሽማግሌ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም፡፡ አስታራቂ ሽማግሌ ባጠፈዉ ላይ ካሳ የሚያሳልፍ እና የቅርታ የሚጠይቀዉን እና የሚጠየቀዉን ወገን የሚወሰን ነዉ፡፡ በተያዘዉ ጉዳይ አማራዉን በባላጋራነት የፈረጁት ቡድኖች አሉ፡፡ እነዚህን ቡድኖች (በወያኔ ፊት አዉራሪነት የሚመሩ) ዕርቅ እናዉርድ ብሎ ድርጅት ማቋቋሙ ተሸናፊነትን የሚያፋጥን ከመሆን ዉጪ ከመዉደቅ እና ከመገፋት አያድንም፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት አራማጆች ህወሓት-ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጀምሮ ስለብሄራዊ ዕርቅ ያላሉበት ጊዜ የለም፡፡ ወያኔ እና መሰል ቡድኖቹ የኢትዮጵያ አንድነት አራማጆችን የድሮ ስርዓትን ከመናፈቅ ጋር እያያዙ በታሪክ አምነዋቸዉ አያዉቁም፡፡ዛሬም ዕርቅ ሰላም እናዉርድ ቢሏቸዉ ጊዜ ከመፍጀት እና ግፉን ከማፋጠን ዉጪ አዲስ ነገር አይኖረዉም፡፡ በተለይ ከአማራዉ ህዝብ የወጡትን የአንድነት አራማጆች ወያኔ እና መሰል ቡድኖቹ እንደጦር ሲፈሯቸዉ ከዛሬ ደርሰናል፡፡ አማራዉ በጥርጣሬ በሚታይበት ወቅት አማራዉ ዕርቀ ሰላም እያለ ቢባዝን ትርፍ ለሌለዉ ነገር መልፋት ነዉ፡፡ እንደ መዉጫ አማራዉ የሚኮራበት እና የሚሞትለት ታሪክ፣ስብዕና መሰረት ያለዉ ህዝብ ነዉ፡፡ አማራዉ በመደራጀቱ እና በመጠናከሩ ሌሎችን ቡድኖች ወያኔን ጨምሮ ለድርድር ማስገደድ ይችላል፡፡ አማራዉ አሁን ያለዉ ብኛዉ አማራጭ ለድርድር ብቁ የሚያደርገዉን ሃይሉን ከማጠናከሩ ላይ ብቻ ነዉ፡፡
እኛ የአማራ ልጆች በኦሮሞ ጉዳይ፣በትግሬ ጉዳይ፣በጋምቤላዉ ሆነ በሌሎቹ ጉዳይ አያገባችሁም፤ እናት ሳለች ሞግዚት ታንቃ ልሙት አለች እየተባለን ከዚህ ስለመድረሳችን ለማሳየት ነዉ፡፡ እዉነታቸዉን ነዉ፤ ቤታችን እያፈሰሰ የእነሱን ቤት ልጠግን መሄዳችን አስመሳይት ነበር፡፡ የጀመርነዉ ጉዞ ተራ ጎዞ አይደለም፤ በምድር ላይ እንደ ህዝብ መቀጠል ያለመቀጠል ጉዳይ ነዉ፡፡ የሃገረ መንግስት(state) ምስረታ በማህበረሰብ ዉል (social contract) የተጀመረዉ ህልዉናን በማስከበር እንደ ህዝብ ለመቀጠል እንጅ ተራ የዳቦ ወረፋን ለማስተካከል አይደለም፡፡ እኔነቴን ካልተቀበለኝ ሰዉ ሆነ ቡድን ጋር ነገን ልቀጥል አይቻለኝም፡፡ ፈርጣማ ክንድ እንዳለኝ ሲያምን በዉዴታ ግዴታ ወደ ማክበር መንገድ ይገባል፡፡ በራሴ ጉዳይ ለዘብተኛ እየሆንኩለት እስካሁን ማንነቴን ሲሰልብ ከቆዬ ከናካቴዉ ህልዉናዬ ብን ብሎ ሳይጠፋ ወደ በረቴ መለስ ብዬ ከወንድሜ ጋር ብመክርና ጎጇችን ከአባታችን አዉድማ ላይ ብንቀልስ የተሻለ ነዉ፡፡ አማራዉ የሚያደራጀዉ ድርጅት የሚሻበት ወሳኝ ወቅት ነዉ፡፡ አገር ዉስጥ ያሉ ድርጅቶች አማራዉን ለማደራጀት እምነት የሚጣልባቸዉም አይደሉም፡፡ እነመኢአድ እና መአድ ቢሆኑም ተዝካር ከማዉጣት የዘለለ መሬት የነካ ተግባር ሲፈፅሙ አላየናቸዉም፡፡ በአናቱ የወያኔን እድሜ በይስሙላ ምርጫ በማራዘም ሰቀቀናችን ያበዙት እነሱ ናቸዉ፡፡ የአማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ግንባር ራሱን ከኤርትራ መንግስት ጫና ነፃ አድርጎ ጎንደር ዙሪያ እንደሰፈረ የሚታወቅ ነዉ፡፡ በሃገር ዉስጥም ሆነ ዉጪ የዚህን ድርጅት ክንፍ መመስረቱና መብዛቱ ለአማራዉ መደራጀት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ አገር ዉስጥ የምንገኝ ሰዎች በቅርብ የምናምናቸዉ እና በፅናታቸዉ እምነት የሚጣልባቸዉን ሰዎች ጋር እየተነጋገርን ጠንካራ የሚስጥር ግንኙነት እንፍጠር፡፡ ይህንን አደረጃጀት በቤተሰብ ደረጃም ማዋቀር እንችላለን፡፡ በአንድ መስሪያ ቤት፣ትምህርት ቤት፣ኮሌጅ፣እና የመሳሰሉ ተቋሞች ቀስ በቀስ የሚስጥር ቡድኖችን ለጥናት ማዋቀርም መደራጀቱን ያፈጥነዋል፡፡ የምንነጋገራቸዉ እና የመደራጀት ዉል የምናስገባቸዉ ሰዎች ለትግሉ ቆራጥ የሆኑ እና እስከ ድል አጥቢያ ለመጓዝ የሚችሉትን ብቻ መሆን አለበት፡፡ የመደራጀት ፍላጎት ኖሯቸዉ ግን እምነት የማይጣልባቸዉ ሰዎች ከሚስጥር ቡድኑ ሳይካተቱ ትግሉን የሚደግፉበትን መንገድ ማመቻቸቱ ተመራጭ ነዉ፡፡ አገር ዉጪ ያላችሁም ሰዎች ሃገር ዉስጥ ካሉ በቤተሰብ፣በጓደኝነት፣አብሮ በማደግም ሆነ በሌላ ሁኔታ ከምትተዋወቋቸዉ ሰዎች ጋር ስለጉዳዩ ግንኙነት በመፍጠር በሃሳብ እና በሌሎች ጉዳዮች እየተነጋገሩ እና እየተረዳዱ መደራጀቱን ማፍጠን ይቻላል፡፡ እንደ መዉጫ እያንዳንዱ ቡድን የራሱን የሚስጥር አስኳል እየፈጠረ መሰሎቹ ጋር ቀስ እያለ በመጠናናት መዋሃድ ይቻላል፡፡ ሁሉንም የሚስጥር ቡድን አንድ የሚያደርገዉ ለአማራዉ ህዝብ ህልዉና መቆም ነዉ፡፡ በህቡዕ የሚደረገዉ መደራጀት የራሱ የሆነ አደጋ የሚኖረዉ ቢሆንም በራሳችን ጉዳይ ያገባናል ብለዉ አለመደራጀት እንደ እግር እሳት የሚለበልባቸዉን ሰዎችን እየመረጡ በማደራጀት የህዝባችን ህልዉና መጠበቅ እንችላለን፡፡
ለአፈር ገፊዉ ህዝባችን እስከቀራኒዮ እንጓዛለን!
ከአማራ ሳይንት