Bete Amhara

Bete Amhara

Monday, June 15, 2015

የአገር አባት መሪ ናፈቀኝ
------------------------
የአገር አባት ናፈቀኝ፡፡ ልጆቸ የሚል መሪ አባት ናፈቀኝ፡፡ እንደ አባት ለልጆቹ የሚያስብ መሪ ናፈቀኝ፡፡ መሪ ራሱ ናፈቀኝ፡፡ መሪ በሌለው አገር መኖር እንዴት ልብን ያደማል! እንዲህ የሚል መሪ አባት ናፈቀኝ “አይዟችሁ ወገኖቸ! የተወደዳችሁ ኢትዮጵያዊያን ሆይ በያላችሁበት በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ስም ልባዊ ሰላምታየ ከዚህ ከከበረውና የህዝብ ከሆነው መንበረ መንግስት ይድረሳችሁ፡፡ ዛሬ የደረሰብንን መከራ ባሰብኩ ጊዜ ማልቀስን ሻትኩ፡፡ ግን መሪ አያለቅስም ብየ ተውኩት፡፡ ግን መሪ አባት ነውና በልጆቹ ፊት እምባን ሲያፈስ ይታይ ዘንድ አይገባም ብየ ተውኩት፡፡ ማዘንና መከፋታችሁን ባየሁ ጊዜ ከባድ ቁጣ መታኝ፡፡ ይህ የደረሰባችሁ በእኔ ዘመነ መንግስት በመሆኑ ሀዘኔ እጥፍ ድርብ ነው፡፡ ልቤ ውስጥ ድንኳን ተክያለሁ፡፡ በዚያም ድንኳን ውስጥ እስከ ቤተሰቤ ለቅሶ ተቀምጫለሁ፡፡ ዛሬ የደረሰብን ውርደት ለበለጠ ክብር ላለው ብሔራዊ ተግባር ይገፋፋንና ያበረታታን እንደሁ እንጅ ጠላቶቻችን እንዳሰቡት ፈጽሞ አንገታችንን ሊያስደፋን አይገባም፡፡ ዛሬ በስማችሁ በተሰየምኩበት ክቡር መንበር ላይ ሆኝ ቃል የምገባላችሁ ማናቸውንም አይነት መንገድ ተጠቅመን ገዳዮቻችንን የገቡበት ገብተን እንደምንበቀል ነው፡፡ አሁን የምናደርገው የበቀል እርምጃ የወደፊት እጣ ፋንታችን ላይ አላስፈላጊ ጉዳት በማያስከትል መልኩ እንዲሆን የተቻለንን ብልሀት ሁሉ እንዘይዳለን፡፡ ጠላት የጽኑ ክንዳችን ኃይል እስኪቀምስ ድረስ ፈጽሞ እንቅልፍ እንደማልተኛ አረጋግጣለሁ፡፡ በቀል የአምላካችን መሆኑን ባንረሳውም እረኛ በጎቹን በክንዱ ብርታት እንደሚጠብቅ የታወቀ ነው፡፡ ይሁንና እረኛ በጎቹን በቻለው መንገድ ሁሉ ከአውሬ መንጋጋ ቢያስጥል በአምላክ ዘንድ ያልተጠላ ነው፡፡ አሁን በዚህ ሰአት ልጆቻችሁ በግፍ የፈሰሰ ደማችንን ለመበቀል በአገራችን ስም ምለው ተነስተዋል፡፡”
ግን እንዲህ የሚል መሪ የለም፡፡ መሪ ራሱ የለም፡፡ በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኘ፡- “ራሴ አንድ ካልሆንክ ብየ ያጉላላሁት አንሶ ያገሬን ሰው በጠላት እጅ እንዲጉላላ አልፈቅድም” ያለው አጼ ቴዎድሮስ ናፈቀኝ፡፡ “እርስ በእርስ እየተመካከራችሁ ጠላት ሳይገባባችሁ አገራችሁን ጠብቁ” ያለው አጼ ምኒልክ ናፈቀኝ፡፡ ጠላትን ገጥሞ ሚስትና እህት ቢማረኩበት እንኳ ልቡ ያልተሰበረው ንጉስ ተክለ ኃይማኖት ናፈቀኝ፡፡ “ኃይማኖት የግል ነው፡ አገር የጋራ ነው” ያለው አጼ ኃይለ ሥላሴ ናፈቀኝ፡፡ “በአንድ ኢትዮጵያዊ አምሳ ሱዳናዊ እጠይቃለሁ” ያለው መንግስቱ ናፈቀኝ፡፡ መሪ ናፈቀኝ፡፡ መሪ ናፈቀኝ፡፡ መሪ ናፈቀኝ፡፡ የህዝቡን እምባ የሚያብስ መሪ ናፈቀኝ፡፡ የህዝቤ ሞት የእኔ ሞት ነው የሚል መሪ ናፈቀኝ፡፡ የምንወደውና የሚወደን መሪ ናፈቀኝ፡፡ ውርደታችን የሚሰማው መሪ ናፈቀኝ፡፡
ከእንብላው በቀር ሌላ የማታውቁት ወያኔና ጀሌዎቹ ግን ገደል ግቡ፡፡ ክፉ እድል እናንተን እዚህ ህዝብ ትከሻ ላይ እንዳስቀመጣችሁ እወቁ፡፡ አይደለም ይህንን ታሪካዊ አገር ልትመሩ ቀርቶ ራሳችሁን አትመሩም፡፡ እናንተ በእኛ አይን ክቡራን ሳትሆኑ ክምራን ናችሁ፡፡ በክፉ ቀን የተሸከምናችሁ ሸክሞች ናችሁ፡፡ እናንተ የሆድ ቁልል ናችሁ፡፡ ዜሮ ህሊናና ጎተራ የሚያህል ሆድ ብቻ የተሸከማችሁ ክብረ ቢስ ፍጡራን ናችሁ፡፡ እናንተን በመስደቤ ከቶ አልቆጭም፡፡ ስዋረድና አንገቴን ስደፋ አልተሰማችሁምና፡፡
የወያኔ ሞት የእኛ ትንሳኤ ነው፡፡ ከወያኔ ጋር የሚቀበረው ውርደትና ማቅ ነው፡፡ ከወያኔ ሞት ጋር የሚቀበረው ለቅሶና ሀፍረት ነው፡፡ የችግራችን ሁሉ ምንጩ ወያኔ ብቻ ነው፡፡ ወያኔ ለአንድ ቀን እንኳ እንዲጨፍርብን ሊፈቀድለት የማይገባ የመሀይማንና የሆዳሞች ጥርቅም ነው፡፡ ወያኔ ከመብላት በቀር ክፉና በጎ ለመለየት ያልደረሱ ድኩማን ፍጥረታት ስብስብ ነው፡፡
ወገኖቸ በርቱ!