Bete Amhara

Bete Amhara

Monday, June 15, 2015

ለሁላችሁም አማራነቴን ለምትክዱ በሙሉ!
-------------------------------------------
በወገናችሁ መንገድ ቆማችሁኋል፡፡ ወግዱ፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ በጣም በሀይለኛ የመከፋት ስሜት ውስጥ ነኝ፡፡ ራሳችሁ አማሮች እኔን ኦሮሞ፡ ወያኔ፡ ሻእብያ ትላላችሁ፡፡ ሞኝ ትሉኛላችሁ፡፡ አማራ አይደለህም ትሉኛላችሁ፡፡ አማራ መሆኔን እንደ ክርስቶስ ካልተሰቀልኩ አታምኑም ማለት ነው፡፡ እሽ ደግ እኔ አማራ አልሁን፡፡ ግን ከፕሮፍ. አስራት ወልደየስ በኋላ ስለእናንተ ደፍሮ የተናገረላችሁ አለ? በ20 አመት ውስጥ እረኛ እንደሌለው ተበትነን አይደለም ያለነው? ሁሉም ማንነታችንን በመካድ እና ሞታችን እንዳይሰማን አይደለም እንዴ የሚታትረው? እኔ አማራን ግደሉ አልኩ? እኔ አማራን ሰደብኩ? የሰደቡትን ተቃውሜአለሁ፡፡ የነቀፉትን ተችቻለሁ፡፡ ያዋረዱትን ረፉ ብያለሁ፡፡ ስለተገደሉብኝ ወንድምና እህቶቸ እንዲሁም እናትና አባቶቸ አልቅሻለሁ፡፡ ያ የልብ ሀዘኔ ስለ አማራ ካልሆነ የተወለድኩባት የአማራ መንደር ሰውነቴን አትቀበል፡፡ የራሴን ምቾት ለአማራ ስል አጥቻለሁ፡፡ በጣም ብዙ ጊዜ፡፡ አሁንም እንቅልፍ አጥቸ፡፡ ሰላም አጥቸ፡፡
ይህም ለአማራ ብየ የማደርገው እንጅ እንደውለታ የምቆጥረው አይደለም፡፡ ግን አማራ አይደለም መባልን ያተርፍልኛል ብየ አላሰብኩም፡፡ እኔ አማራ እንደጠላት፤ መድረሻ እንደሌው ደሀ የሚቆጠረው በስህተት ነው፡ ሃብታም ነው፡ ራሱን ይችላል ነው ያልኩት፡፡ እንደመጻተኛ ተበትኖ መድረሻ ያጣውን ወገናችንን ሰብስበን ሀብት እንኳ ብናጣ ድህነትን በሰላም ተካፍለን መኖር እንችላለን ነው ያልኩት፡፡ አማራ ለዚህች አገር አንድ ህዝብ ሊከፍል አይደልም ሊያስብ ከሚችለው በላይ አድርጓል እና እንደበጎ ስላልታየለት የራሱን ቤት ይስራ ነው ያልኩት፡፡ አማራ ዜግነት ስላጣ ዜግነቱ ይመለስለት ነው ያልኩት፡፡ አማራ አገር አልባ ስለተደረገ አገር ይኑረው ነው ያልኩት፡፡ አማራ ምድሩ ሁሉ ተሸንሽኖ ተወሰደበት፡ ተሸጠበት፡፡ እርሱም ይመለስለት ነው ያልኩት፡፡ የተካደውን ማንነቱን ለመገንባት እንዲሁም የውሸት ክህደትን ለማፍረስና ማንነታችንን ተክዶ እንዳይቀር ለማንሳት ነው እየጣርኩ ያለሁት፡፡ አማራ ጠላቱ በዝቶበታል ስለሆነም ጨርሶ ሳይጠፋ ራሱን ያትርፍ ነው ያልኩት፡፡ ለወደፊት ልጆቹ ቤት እንስራለት፡ የአባቶቻችን የዋህነት ይቁም ነው ያልኩት፡፡ አማራ አገር ለመሆን ብቃትም፡ ምክንያትም፡ ሀብትም፡ ሁሉም ነገር አለው ነው ያልኩት፡፡ የራሴን ህይወት ወደጎን ትቸ ነው እየለፋሁ ያለሁት፡፡ ለዚህ ስራየ አንዳችሁም ሻይ እንኳ አላላችሁኝም፡፡ ይህን ማሎቴ እንዴው ልፋቴን ለማሳወቅ እንጅ ከወገኔ ጉቦ ፈልጌ አይደለም፡፡ የሚናገርለት ለሌለው ወገኔ ገና ልሞትለት ነው እንኳን ይህን ማድረግ፡፡ ግን እንዴት እናንተ እኔን በዚህ ሁሉ ስራየ የአማራ ልጅነቴን ጥያቄ ውስጥ ከተታችሁት?
ለእናንተ እንደዚህ ለምታጎሳቁሉኝ ስል ሁሉንም ትቸ የራሴን ህይወት መኖር እችል ነበር፡፡ ለእናንተ ስል እንደማንም ፎቶየን እየለጣጠፍኩና አልፎ አልፎ አንበሳ ያለው ባንዴራ እያደረግኩና የስፖርት ምስል ያእደርገኩ መኖር እችል ነበር፡፡ ግን ያስተማሩኝ ወገኖቸ የሚናገርላቸው የለምና ለእነሱ መናገር አለብኝ፡፡ ከደግነት በቀር ምንም የማያውቁ ግን ጠላታቸው የበዛ ወገኖች አሉኝ እና ስለእነሱ ዝም ማለት አልሆንልህ አለኝ፡፡ ስነሱ የሚናገር ባለመኖሩ ለመናገር ቢነሳም ስለሚታፈን ያንን ለማስወገድ ነው ልፋቴ፡፡ የምታፍኑት እናንተም ናችሁ፡፡ የታፈነ ህዝብ ልጅ ነኝ፡፡ ዝም እንዳልል ህሊና አለኝ፡፡ ወገኔን ባልናገርለት ህሊናየ ይወቅሰኛል፡፡ ባጭሩ ተውኝ፡፡ አለመናገር አልችልም፡፡ የማልችለውን ነገር አድርገ ብላችሁ አታስቸግሩኝ፡፡
ግን አንድ ቀን ትክክል እንደሆንኩ ታውቃላችሁ፡፡ በዚህ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ምናልባት ትጸጸቱ ይሆናል፡፡ የኔን ያህል ስለአማራ የሚናገርላችሁ የሌላ ወገን ቢኖራችሁ ኖሮ ጠላት እንደሌላችሁ አውቅ እና መናገሬን አቆም ነበር፡፡ ግን አልመሰለኝም፡፡ የእኔን እና የጓደኞቸን ያክል የሚናገርላችሁ ቅጥረኛ ካለ እውትም የልብ ወዳጃችሁ ይበዛል ማለት ነው፡፡ ልብ ይስጣችሁ፡፡
መለክ ሐራ ከቤተ አማራ!
ድል ለቤተ አማራ!