አሁንም አንድነት ስለምትሉ የቤተ አማራ ወገኖች
እናንተ ሌላውን በማቆላመጥ የምታመጡት አንድነት ብሎ ነገር የለም፡፡ ከአንድነትም የምትጠቀሙት ነገር እንደሌላ እስካሁን የተገነዛበችሁት አይመስልም፡፡ አማራን አምላክ ነው የኢትዮጵያ አንድነት ወኪል ያደረገው? ይሄ በመሰረቱ ሌሎችን ነገዶች መናቅ ነው፡፡ እኛ ብቻ ነን የአንድነት ተቆርቋሪ ስትሉ የሌሎችን ሀላፊነትና ስሜት መቀነሳችሁ ነው፡፡ማንም በጋራ ስለሚኖረበት አገር እኔ ብቻ ነኝ የኢትዮጵያ አንድነት የሚመለከተኝና የምታደጋት የሚለው የተንሸዋረረ እይታ ነው፡፡ ለሌሎች እድል እንዳላቸው እወቁ፡፡ ደግሞ ይህ አዝማሚያ ወደረኞቻችን ትምክህት ብለው የሚነቅፉት ነው፡፡ ይህም ትምክህት የራስን እንትን ገልቦ ሌላውን ካላጎናፀፍኩህ የሚል አጉል ስራ ነው፡፡ አያቶቻችን የራሳቸውን ህዝብ እየበደሉ ሌላውን አካባቢ ሲያበለጽጉ ነው የኖሩት፡፡ የራሳቸውን ህዝብና ምድር ከወታደር መመልመያነት ባለፈ አስበውት ቢሆን ኖሮ ዛሬ መሳለቂያ አንሆንም ነበር፡፡ ቤተ አማራ የአያቶቻችንን ስህተት የሚያርም እንጅ የሚደግም አይደለም፡፡ ይህ አንድነት አንድነት የሚል አሰልች ነገር ነው ወገናችንን የተለየ ተጠቃሚ በማሰመሰል እንዲታረድ ያደረገው፡፡
አላወቃችሁትም እንጅ ይሄ አጥብቃችሁ የምትወዱት ሰፊ መሬት የእናንተ አይደለም እኮ፡፡ በኢትዮጵያ ስርም ሆነ ለብቻው ሆነ ለእናንተ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ የሚጠቀምበት እዛው ላይ የሰፈረበት ሰው ነው፡፡ ይህም እናንተን የመሬት ካርታ ቅርጽ እንጅ ትክክለኛ እንድነትን ወይም የአማራን ህልውና አደጋ በውል ያለመረዳታችሁን ነው የሚያመለክተው፡፡ ቀደም ብሎ የአገር አንድነት በአማራ ኪሳራ እንዲገነባ ሆኗል፡፡ አሁንም እናንተ የምትፈልጉት አገር በአማራ ኪሳራ ላይ አንድ ሆኖ እንዲቀጥል ነው፡፡ ቤተ አማራ ደግሞ በአማራ ሞት ላይ የምትጸናን አገር ማየት አይፈልግም፡፡ ስለአንድነትም አያቶቻችን የከፈሉት ይበቃል፡፡ ያ ልፋታቸው መና እንደቀረ አይተናል፡፡ የልጅ ልጆቻቸው እስከነፍሳቸው ሲታረዱበትና ሲቃጠሉበት በአይናችን በብረቱ እያየን ነው፡፡ መቃብራችንን እንድንጠብቅ አታስገድዱን፡፡ በጊዜ የምንኖርበትን ቤት እንስራ ይልቅ፡፡
እኔ እናንተን ብሆን እንዲህ ነበር የማስበው፡፡ የአማራ ራሱን ነጻ መንግስት የማድረግ ሂደት እናንተ ለምትፈልጉት አንድነት ምናልባት ሊጠቅም ይችላል፡፡ ይሄም ማለት ሽህ ጊዜ አንድነት አንድነት ማለት ምንም የፈየደው ነገር ስለሌለ በአማራ መጠናከር ሳቢያ አንድነትን መሻት ይቻላል፡፡ ይህም ማለት ሌሎችን ነገዶችም አገራቸው የአማራ ብቻ እንዳልሆነና የራሳቸውም እንደሆነ ብሎም የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲወጡ ያደርጋል፡፡ ይህም በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ እውነተኘ አንድነት ሊያመጣ ይችላል፡፡ ያም አንድነት ማንም ማንንም እየከሰሰ የማይኖርበት፤ ሁሉም ለሀገሩ የኔ ብሎ በተቆርቋሪነት የሚሰራበት፤ አንዱ ሲጥር ሌላወ የማይተኛበት አገር ለመፍጠር ያስችላል፡፡ አሁን ግን ስለአንድነት ተብሎ አማራው እየታረደ ይቀጥል የምትሉትን ነገር ቤተ አማራ ፈጽሞ አይቀበለውም፡፡ ቤተ አማራ የእናንተን በአንድንት ጥላ ስር እንቆይ የሚለውን ጥያቄ የሚቀበለው የህዝባችንን ደህንነት ማስጠበቅ የሚችል አስተማማኝ ምላሽ ቢኖራችሁ ነበር፡፡ ያ ደግሞ የላችሁም፡፡ እንዲሁ በቃል ደረጃ አንድ ሆነን እንኑር ከማለት የዘለለ ህዝቡን ከጥፋት የሚታደግ ምንም ነገር ማምጣት አትችሉም፡፡ ከቻላችሁስ ከስንት አመት በሁዋላ? ከመቶ አመት በሁዋላ? ህዝቡ ካለቀና ምድራችን ባዶ ባድማ ከሆነ በኋላ? ወይስ ህዝባችን ሳያልቅ? እነዚህን ጥያቄዎች በደንብ ስታጤኗቸውና አቅማችሁን ስታገናዝቡ የቤተ አማራን ውሳኔ እንደምትቀበሉ ጥርጣሬ የለውም፡፡ እኛም ይህንና መሰል ጥያቄዎችን ስናሰላስል ከርመን ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስነው፡፡ ደግሞስ በደምና አጥንቱ ለገነባት አገር ዜግነት የተነፈገ ህዝብ ለምን ብላችሁ ነው እንደገና አንድ ሆነህ እየጠፋህ ጠብቅ ይምትሉት? የእናንተም እኮ አላወቃችሁትም እንጅ ለከፋ በደል እንዲጋለጥ ማድረግ ነው፡፡ ደግሞስ 40 አመት ሙኩ ለተነዛበት የጥላቻ ስብከት ስንት አመት ይበቃችኋል የጥላቻውን መርዝ ለማክሸፍ? መቶ? ሁለት መቶ? እናንተ እስክትደርሱለትስ ይህ የተነዛ የጥላቻ መርዝ ጨርሶ ከገፀ ምድር እንደማያስወግደው ምን ማረጋገጫ አላችሁ? ሳይመሽ አስቡበት፡፡ እናንተ አንድነት ላይ ሙጭጭ በማለታችሁ ነው እኮ አማራው የሚልሰው የሚቀምሰው እንደሌለው የሚያስቆጥረውና የሚያስንቀው፡፡ አማራ አንድነት አንድነት የሚለውም ለራሱ ጥቅም ነው ተብሎ እንዲታሰብ የምታደርጉት፡፡ ከቻላችሁ ኢትዮጵያን ከአማራ ሸክምነት አውርዷትነ ለሁሉም እኩክ አካፍላችሁ አሸክሟት፡፡ አማራ ብቻውን ታከተው፤ ደከመው፤ አልሆንልህ አለው፡፡ ይባስ ብሎም መታረጃውና መቀበሪው ሆነች፡፡ ተሸክሟት በኖረ መቃብሩ ሆነች፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ ሆድን የሚስብስና ለእልህ የሚያነሳሳ ነገር ሊሆን በተገባ ነበር፡፡
አሀንም እናንተን ብሆን ስለቤተ አማራ እንዲህ ነበር የማስበው፡፡ አማራ የራሱን መንግስት የማቋቋሙን ነገር በገፋበት ቁጥር አገዛዙ በውጥረት ምናልባት የቤተ አማራን ዜግነት ሊመልስ ይችላል፡፡ ከተነሳሳበት የጥፋት እርምጃ ይቆጠብ ይሆናል፡፡ አማራውም ያኔ አገር ይኖረው ይሆናል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች እስከ መገንጠል ፀንተው በሚሄዱ እርምጃዎች ሊመለሱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም ህዝቡን ከእልቂት እንታደጋለን፤ አንድ የምንለውንም አገር እናስጠብቃለን፡፡ ይህ ነበር መሆን የሚገባው የእናንተ ግንዛቤ፡፡
ቤተ አማራ ግን እምነቱ አማራው የራሱን ቤት አጥሮ ሀብት እንኳ ባይኖረው ድህነትን እኩል ተካፍሎ በሰላም የሚኖርባትን አገር መፍጠር ነው፡፡ እድሜ ልክን እየተሰደቡ እየተንቋሸሹ መኖር ይበቃል፡፡ ከቻላችሁ የቤተ አማራን መንግስት ለመመስረት የምናደርገውን ጥረት እርዱን፡፡ ካልቻላችሁ ደግሞ መንገዳችን ላይ ባትቆሙብን ለእናንተም ከጸጸት መዳን ለእኛም የእንቅፋት መቀነስ መሆኑን እወቁት፡፡ አንድ የሚባል አገር ካስፈለገ እንኳ መጀመሪያ የራሳችንን ማረፊያ ይዘንና ደህንነታችንን አስጠብቀን ተደራድረን አንድ አገር መፍጠር እንችላለን፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ግን አንድነት ብሎ ሙጭጭ ማለት ህዝብን ለተጨማሪ ጥፋት ከመዳረግ በቀር የሚያመጣው አንዳች ትርፍ የለም፡፡ በኪሳራችን አትደራደሩ፡፡ ይህ ነው የሚባል አመርቂ ህዝብን ታዳጊ ዘዴ እስካላመጣችሁ ድረስ የእናንተ የአንድነት ንግግር ምንም አይዳ የሌውና በህልውናችን ላይ ለሚደረገው ጥፋታዊ እርምጃ ተባባሪ መሆን ነው፡፡ መጀመሪያ ራሳችሁን አድኑና ከዛ ሌላው ነገር ይደረስበታል፡፡
በአማራነታችሁ ብቻ ተሸብባችሁ እንደትቀመጡና የአቅማችሁን አስተዋፅኦ በማድረግ ልታሳድጓት የምትፈልጓትን አገር መርዳት አልቻላችሁም፡፡ ለ23 አመታት ተቀይዳችሁ ቁጭ አላችሁ፡፡ አገሪቱም የመሀይም መጫወቻ ሆነች፡፡ በዚህም ከአለም ሁሉ ጭራ ወይም ሁለተኛ ደሀ አገር ሆነች፡፡ ምን ፈየዳችሁ? ብዙዎቻችሁ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ መቀየር የሚችል አቅም እንዳላችሁ ይታወቃል፡፡ ግን ማን ፈቀደላችሁ? ማንም፡፡ ወጣትነታችሁም እውቀታችሁም ምንም ሳይፈይድ መና ሆኖ ቀረ፡፡ ስለዚህም በቤተ አማራ እምነት እውቀታችንን ሊጠቀምበት ቀርቶ እንደጠላትነት ለምትወስድ አገር መኖርም ሆነ መሞት አላስፈላጊ ነው፡፡ ይህንን ወጣትና እውቀት ጨርሶ መና ሆኖ ከመቅረቱ በፊት የቤተ አማራን መንግስት ልንገነባበት እንሻለን፡፡ እንዲሁ በከንቱ አፈር ከሚበላው ለወገናችሁ ብታውሉት እንወዳለን፡፡ ካልተፈለጋችሁ ወደምትፈለጉበት ህዝብና አገር መሄድ ነው ምርጫው፡፡ እንዲሁ ቁጭ ብላችሁ አንገት ደፍታችሁ እርጅናን በድህነት ከመጠባበቅ በቀር የምታመጡት ጠብ የሚል ነገር እንደሌለ ራሳችሁም ታውቁታላችሁ፡፡
ደግሞስ ምድራችሁ ተባብራችሁ በአገርነት ከመሰረታችሁት እኮ ሀያል መንግስት ለመሆን በቂ ነው እኮ፡፡ ያለ የሌለ ሀይላችሁን እና አቅማችሁን ብትጠቀሙበት ባጭር ጊዜ ወገናችሁን ከመከራ ታላቅቃላችሁ፡፡ ሀያል አገርም መፍጠር ትችላላችሁ፡፡ ለቤተ አማራ መስራት እኮ በፖለቲካ አመለካከታችሁ የማትገለሉበት፤ ለወገናችሁ እንድትሰሩ የምትበረታቱበት ነው፡፡ መስራት የምትፈልጉትን ሰርታችሁ ለወገናችሁ ብርሀን ሆናችሁ ታልፋላችሁ፡፡ በቤተ አማራ ጥላ ስር የተሰባሰብን ወጣቶችም ለወገናችን ያለንን ሁሉ ሳንሰሰት አድርገን በላባችን የምንከበርባትን ቤት መስራት ነው፡፡ አሁን ባለው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያሰራን የለም፡፡ የሚያግደን እንጅ፡፡ ስለዚህ አቅምና ጉልበታችንን እንዲሁም እውቀታችንን አበክሮ ለሚሻው ወገናችን እንስጠው፡፡ ከጉስቁልናና ከስድብ እንታደገው፡፡
ድል ለቤተ አማራ!