Bete Amhara

Bete Amhara

Tuesday, July 14, 2015

የተማርኩብሽ ጎንደር

የተማርኩብሽ ጎንደር 
……….

አንድ ከሰአት ለአባቴ “ዩኒቨርሲቲ እኮ ጎንደር ደረሰኝ፡ ጎንደር የሚባለው አገር እንዴት ነው” አልኩት፡፡ እርሱም ደስ አለው፡፡ “ጎንደር ሀይማኖተኛ፤ እንግዳ አክባሪ አገር ነው” አለኝ፡፡ በስራ ምክንያት የተወሰነ ጊዜ ጎንደር ላይ ቆይቷል፡፡ እናም አለኝ አባቴ “ከአንድ ጎንደሬ ጋር እየሄድክ አንተን አንድ ሰው ቢጣላህ መጀመሪያ የሚመመታው አብሮህ ባለው ሰው ነው፡፡ አብሮህ ያለው ሰው ለምን ለአንድ ደቂቃ ይሆንም የተዋወቅከው ብቻ እኔን ነው የደፈረኝ ብሎ ነው የሚያቀምስልህ” አለኝ፡፡
……….
የትውልድ ቦታየ ከጎንደር 800 ገደማ ኪሎ ሜትር ትርቃለች፡፡ በደስታ እና ከቤተሰብ በመለየት መንፈስ ሆኘ ወደ ጎንደር ተሸኘሁ፡፡ ከዛ በፊት ጎንደር በፎቶና በቴሊቪዥን የማውቃት የፋሲል ግንብ ብቻ ትመስለኝ ነበር፡፡ ዙሪያዋን ብዙ ቤት የሌላት ትመስለኝ ነበር፡፡ ምንም እንኳ የኔዋ ትውልድ ቦታ ትንሽ የገጠር ከተማ ብትሆንም ወደ ገጠር እንደገና የመሄድ ስሜት እየተሰማኝ ሄድኩ፡፡ ጎንደር የታሪክ ብቻ ከተማ እንጅ አሁን ትልቅ ከተማ አይደለም ብየ አሰብኩ፡፡
……….
ግን ልቤ በሲቃ የምትመታበት ነገር ነበራት፡፡ ብትህምርት ቤት የተማርኩትን እና ያነበብኩትን ታሪክ በአካል ላየው ነው፡፡ ቁስቋምን፡ ፋሲል ግቢ የሚገኙ አብያተ መንግስታትን፤ ቆብ አስጥልን፤ አዘዞ ተክለ ሀይማኖትን እና ደብረ ገነት ኢየሱስ (የሀይማኖት ግጭት የተከሰተበትን ቦታ)፤ የሰመመኑን አቤል ከተማ፤ ራስ ግምብን፤ ደብረ ብርሀን ስላሴን፤ እና እንቁላል ግንቦችን፡፡ በተለይ ደግሞ የሚዘፈንለት ጎንደር እንደዘፈንዋ ናትን የሚል ጥያቄ በውስጤ እያንሰላሰልኩ፡፡ ዘንተራን ማለትም በቱርክ የታገዘው የግራኝ ጦርነት የተገታበትን ወይና ደጋን አስታውሳለሁ፡፡ ስለ አበቄሽ ጎንደር ሰምቻለሁ፡፡ ስለ መዋኛ ገንዳው ሰምቻለሁ፡፡ የታንጉት ምስጢርዋን ደበክ ደበክ የምትለውን ደጋግማ “ኧረ ባባጃሌው” የምትለውን ሴት በምናቤ አሰላስላለሁ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የወደቀበትን ሁኔታና ማን ለዛ እንደዳረገን አስታውሳለሁ፡፡ አንገረብ የተባለውን ወንዝ በዝና አውቀዋለሁ፡፡ በደርቡሽ ጦርነት የደረሰባትን መአት አስታውሳለሁ፡፡ በ1704 የመሬት መንቀጥቀጥ እንደመታት አንብቤያለሁ፡፡ በተለይ ጠጭዎች አሁንም ድረስ የአበቄለሽን ወንበር እየተወለጋገዱ እንኳ ለጥ ብለው እጅ ነስተው “እሜቴ ይማሩኝ” እንደሚሉ አስታውሳለሁ፡፡ ቤተ መንግስቱ ሶስተኛ ፎቅ ላይ በቀጥታ ከጣና ነፋስ የሚገባባት መስኮት እንዳለች ሰምቻለሁ፡፡ ንጉስ ፋሲለደስ ከቤተ መንግስታቸው በምስራቅ በኩል ካለው ተክለ ሀይማኖት ቤተ ክርስቲያን በቀስተ ደመና ድልድይ እንደሚመላለሱበት አስታውስ እና እገረም ነበር፡፡ በቀስተ ዳመናው ስርም ያለው መንገድ ቆብ አስጥል እንደሚባል ሰምቻለሁ፡፡
……….
ስለ አስራሁለቱ የፋሲል ግቢ በሮች ታሪክም ሰምቻለሁ፡፡ እነሱም እጨጌ በር፤ አደናግር በር፤ እርግብ በር፤ ዣንጥራር በር፤ አዛዥ ጠቋሬ በር፤ ኳሊ በር፤ ፈረስ ባልደራስ በር፤ አደናግር በር ወዘተ አስታውሳለሁ፡፡ የቋረኞች መግቢያ፤ የሸዋ ማረፊያ፤ የትግሬ ማረፊያ፤ የስሜን በር ወዘተ ይናፍቁኛል፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ጋር ተዋግታ አመድ ሆና የተሸነፈቸው ጎንደርም ትዝ ትለኛለች፡፡ በአንድ ለእናቱና በታንጉት ምስጢር እንዲሁም በሰማኋቸውና ባነበብኳቸው መጽሀፍት ሰፊ ምናባዊ ጉብኝት ያደረግኩባት ጎንደር በልቤ ታትማ ቀርታለች፡፡ ከ”ባላገር” ጋር ሰንበቴ ማህበር ይጠጡ የነበሩትን የጎንደር ንጉስ አስታውሳለሁ፡፡ ሙዚቃ የሚወድ ዮሐንስ ሶስተኛ የተባለ ንጉስ እንደ ነበራትና አንድ የመጽሀፍት ቤት ግቢው ውስጥ እንዳሰራ ሰምቻለሁ፡፡ ዞብለው የተባለው የፋሲል የፈረስ ቤት እስካሁን እንደሚገኝ ሰምቻለሁ፡፡ የንጉስ ፋሲል የእንቁላል ወይም ዶሮ ርቢ ዘመናዊ ቤት እንደነበረ ሰምቻለሁ፡፡ ማስተር ወልደ ጊዮርጊስ የተባለ የፖርቱጋሎችን ጥበብ ወርሶ ጎንደርን የገነባ አማራ መሀንዲስን ታሪክ አንብቤያለሁ፡፡ ጀምስ ብሩስ የተባለ ስኮትላንዳዊ በአለም ላይ ጠፍቷል ተብሎ የተደመደመለትን የሄኖክ መጽሀፍ ከጎንደር እንደወሰደና በእንግሊዝ አገር ሲያሳትመው በዘመኑ በገበያ ተወዳዳሪ እንዳልተገኘለት አንብቤያለሁ፡፡ የፈረንሳዩ ጀምስ ፖንሴት በመጠባት ዘመን በመስታዎት ስራ ጥበብ የተካኑ አማሮችን እንዳየ ጽፎ አንብቤያለሁ፡፡
……..
ያች የቦታ የአማራ ዘር ከጥፋት የዳነባት፤ የአማራ ታሪክና ክብር ከወደቀበት እንደገና ከፍ ያለባት እንደሆነች አንብቤ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ ጎንደር በተለምዶ የአፍሪካ ሻኛ ተብላ እንደ ምትጠራ አውቃለሁ፡፡ እንደገናም አማራ የወደቀባት እንደሆነች አውቃለሁ፡፡ እንደገናም እንደተነሳባት አውቃለሁ፡፡ እኛ አማሮች ጎንደር ላይ ሁለት ጊዜ ወድቀን ሁለት ጊዜ እንደተነሳን እገነዘብ ነበር፡፡ አሁን ላይ ሳስበው አማራ ለሶስተኛ ጊዜ ጎንደር ላይ ይነሳ ይንን እላለሁ፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ ከተነሳን ከእግዲህ እንዳንወድቅ ዘዴ ዘይደን ለትውልድ አስተምረን እናልፋለን ብየም አስባለሁ፡፡
………
ሰክሮ በጨለማ የንጉሱን ኢያሱን በቅሎ ካልገዛሁ ብሎ የተገለገለ ሰው ታሪክ አውቃለሁ፡፡ ንጉሱም “ሂዱና መግቢያውን እዩት” ማለቱንና በማግስቱም ስካሩ ሲለቀው አስጠርተው “እንካ ግዛት ይችን በቅሎ” ቢሉት እርሱም ከጓደኞቸ ልማከር ማቱን፤ ንጉሱም “ማታ ስናይህ ብቻህን ነበርክ” ሲሉት “አይ አይደለም ብቅልና ጌሾ አብረውኝ ነበሩ” ብሎ መልሶ በሳቅ እንደታለፈ አንብቤያለሁ፡፡
…….
ጎንደር ሀብታም አገር መሆኑን በተለይም እጣን፤ ጥጥ፤ ሰሊጥ እና እህል በያይነቱ አምራች እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ሰውም ለጋስ፤ እንግዳ ተቀባይ፤ ቁጡ እና የሰው ክብር አዋቂ እደሆነ ሁሌ የምሰማው ነገር ነበር፡፡ አብሮ የሚበላ፤ ጨዋ እና ባህሉን ወዳድ እንደሆነ አባቴ ዘወትር የሚነግረኝ ታሪክ ነው፡፡
…….
ከዘፋኞችዋ ብዛት የተነሳ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ የመሩት እና ጫፍ ያደረሱትን የትውልድ ቦታ ለማየት እናፍቀለሁ፡፡ የይርጋ ዱባሉ፤ የአስቴር አወቀ፤ የፍቅር አዲስ፤ የፋሲል፤ የአበበ ተካ፤ የእንደልቤ፤ የማናልሞሽ፤ የገነት፤ የአምሳል እና ሌሎችን በርካታ ዘፈኞች አገር ለማየት እጓጓለሁ፡፡ የአማራን ስነልቡና በመገንባት እነዚህ ዘፋኞች ትልቅ ውለታ ውለዋልና የተወለዱባት ምድር ትናፍቀኛለች፡፡
……….
ስለጎንደር ሳስብ ዘወትር በአእምሮየ የሚመጡብኝ በታሪክ የማውቃቸው ስፍራዎች ዛሬም የመንገዴ አጃቢዎች ሆነዋል፡፡ ወገራ ዳባት፤ ቸንከር ተክለ ሀይማት፤ አዳኝ አገር ጫቆ፤ ጃኖራና ራስ ደጀን፤ አምባ ጊዮርጊስ (ጋረድና ቴዎድሮስ ትልቁን ጦርነት ያደረጉበት)፤ ደረስጌ ማርያ፤ ደባርቅ፤ ማይጠምሪ፤ አዳርቃይ፤ ጠገዴ፤ ወልቃይት፤ አርማጭሆ፤ ዳንሻና ሁመራ፤ መተማና ቋራ፤ ጭልጋ፤ ደምቢያና ጣና እንዲሁም ቆላድባና ጎርጎራን፤ አለፋ ጣቁሳ፤ እንፍራዝና በለሳ፤ አዲስ ዘመንና ፎገራ (የአባ ገብረሀና አገር)፤ ወረታና ጋይንት፤ ክምር ድንጋይና ነፋስ መውጫን፤ ደብረ ታቦርን እና ወረታን አስታውሳለሁ፡፡ እነዚህ ቦታዎች በታሪክ ተደጋግመው የሰፈሩ በመሆናቸው የኖርኩባቸው ያህል ነው የሚሰማኝ፡፡
……..
በመንገዴ ላይም የማስበው ይሄንን ሁሉ ለማየት እና ምን ያህሉን ቦታ እንደተባለለት በቦታው አገኘዋለሁ በማለት ነበር፡፡ አዲስ ዘመንን፤ እፍራዝን፤ ማክሰኝትን፤ ጠዳን አልፈን በአዘዞ አድርገን ጎንደር ደረስን፡፡ ጎንደርን አየኋት፡፡ ስደርስ ጨልሞ ነበር፡፡ ማራኪ ላይ ሆኘ ጎንደርን አየኋት፡፡ እንቁጣጣሽ መስላለች፡፡ የሌሊት አበባ፡፡ በሲቃ ተዋጥኩ፡፡ ይች ጎንደር ናት፡፡ አወ ጎንደርን አየኋት፡፡ አወ ከእንግዲህ ጎንደር ገብቻለሁ፡፡ በቀጣይ አራት አመታት እዚህ እከትማለሁ ማለት ነው፡፡
………
እየዋልኩ እያደርኩ ጎንደርን እየበረበርኩ እጎበኛት ጀመር፡፡ ታክሲ ውስጥ ከማገኛቸው ሰዎች መካከል ዘመዶች አፈራሁ፡፡ ወደ ምግብ ቤቶች ስሄድ የማገኛቸው ሰዎች ወዲያው ጓደኞቸ ይሆናሉ፡፡ ሲያስተናግዱ የእህት እንጅ የንግድ አይመስልም፡፡ የጎንደር ልጆችን ተዋወቅሁና ሁልጊዜ አመትባልን፤ ክርስትናን፤ ማህበርን እና ሰርግን እያሳደድኩ መታደም የየለት ስራየ ሆነ፡፡ አንድ የሚገርመኝ ነገር የጎንደር ሰው ከተዋወቀህ ቀድሞ የዛሬ ሶስትም አራትም ወር ሊሆን ይችላል “የሆነ ድግስ አለኝ እና እንዳትቀር አደራ፤ የቀረህ እንደሆን እንኳን በምድር በሰማይ አንገናኝም ነው” የሚልህ ነገር ነው፡፡ ሰው ጨዋታ አዋቂ፤ እጅግ ትሁት…
………
አንድ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ አመጽ ተነሳ፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ጥርግ ተደርገን ተባረረን--ለሰባት ቀን ያህል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ታዲያ በቤተ ክርስቲያን ለተሳላሚው ተማሪ እንዳያስጠጉ ለፈፈ፡፡ የጎንደር ሰው ግን ሸሽጎ እቤቱ እያሳደረ እያበላ እያጠጣ ክፉ ቀንን አሳለፈልን፡፡ በደርግ የጎንደር ወጣቶች በኢህአፓነት እየተለቀሙ ሲረሸኑ ወላጆች የሌላ ክፍለ ሀገር ተማሪዎችን እቤታቸው ደብቀው ልጆቻቸውን “አንተ አገር ታውቃለህ ሂድና ተደበቅ፤ ይሄ ግን የሰው አገር ሰው ነው” ብለው ልከው እንግዳዎችን ደብቀው እንዳተረፉ ራሱ የዚህ ታሪክ ውለታ የተደረገለት የሌላ አካባቢ ሰው አጫውቶኛል፡፡
………
ታሪኬን አየሁ፤ ሰማሁ፤ በአይኔ ታዘብኩት፡፡ በውኑ ከሰማሁትና ካነበብኩት በላይ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ድሮ ግንቡ ብቻ ይመስለኝ የነበረው ጎንደር አሁን ሳየው በነበረኝ ቁንጽል ግምት በጣም አፈርኩ፡፡ ለካ ጎንደር ልጥጥ ያለ ሰፊ ከተማ ነው፡፡ ወዲያውም በዛን ጊዜ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ትልቁ ከተማ ነው ተብሎ ተነገረኝ፡፡ ጎንደር ትልቁ አገር፡፡ ጎነደር ትልቁ የአማራራ እምብርት፡፡ አራት አመት ኖርኩበት፡፡ እስካሁንም ድረስ ብዙው ነገር በአይኔ ውል ውል ይልብኛል፡፡ አመት በአል ተጠርቶ መሄድ፤ “በሞቴ አፈር ስሆንልህ፤ በአንድ እጨት ስሄድ” እየተባሉ ጉርሻና ዳረጎት ይናፍቀኛል፡፡ በእድሜ አያቴ የሚሆን ሰው እንኳ መቀመጫ ለቆ እኔን ተቀመጥ የሚለኝ ትውስ ይለኛል፡፡ ብዙ የድሮ ግንብ ፍርስራሾች በብዙ ቦታ እደነበሩ አወቅኩ፡፡ ደርቡሽ፤ ጣልያን፤ የእግሊዝ ድብደባ እና የመሬት መንቀጥቀጥ እዲሁም የዘመነ መሳፍንት ስርአተ አልበኝነት ባያጠፏት ኖሮ ጎንደር የጥንቷ ትልቅ አበባ ከተማ ነበረች፡፡ በተለይ የጥንት ገጽታዋን በአይነ ህሊናየ ስስላት በጣም እንገበገባለሁ፡፡
……..
ምሽት ቤቶች እነ ላንባዲና፤ ዲሰንት ፓብ፤ ብርቧክሶች የባህል ምሽት ቤት፤ ቋራ ሆቴል፤ ሰርክል ሆቴል፤ ተራራ ሆቴል፤ ሀበሻ የባህል ምግብ ቤት፤ ጃን ተከል ዋርካና መናፈሻው፤ ጉዛራ መናፈሻ፤ ሳሙና በር ያሉ መዝናኛዎች፤ ብሪጅ እስራኤል መዝናኛ፤ ወዘተ ውል ይሉብኛል ዛሬም፡፡ ቴዎድሮስ ካምፓስ፤ ማራኪ ካምፓሰ፤ ጀሲ ካምፓስ ዋና ዋናዎቹ ካምፓሶች…..እያንዳንዳቸውን እየተመላለስኩ ኖርኩባቸው፡፡ ቀነኒሳ ጫት መሸጫ የሚባልም ነበር፡፡ አንድ ቀን “አምጣ ይሄን የአማራ ጫት” ብሎ በጥላቻ ሁኔታ ተናግሮ በጥፊ የተመታ ሰውም እንደነበር አይቻለሁ፡፡ ከጎንደር ልጆች ጋር ሆነን አስራ ስምንት ወይም ልደታ እየሄድን ጠጥተን ሰክረን ስንገባ እደነበረ የዛሬ ትዝታየ ነው፡፡
……..
አንድ ጊዜ ትንሽ ራቅ ወዳለች የገጠር ከተማ አንዱ ጎንደሬ ጓደኛችን ሰርግ አለ እህቴ ትዳራለች ብሎ ወሰደን፡፡ ከዛ ሄደን የተደረግልንን መስተንግዶ መቸም አልረሳውም፡፡ ዳሱ ለሁለት ተክፍሎ ስናይ ጊዜ ምን እንደሆነ ጠየቅነው፡፡ እሱም በአገጩ እያሳየ “ያኛው የሙስሊም ክፍል ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ክርስቲየያኑ ነው” አለን፡፡ እርስ በርስ እየተገረምን ተያየን እና እዲያብራራልን ጠየቅነው፡፡ እርሱም እንዲህ አለን፡፡ በኛ አገር ሰርግ ወይም ሌላ ድግስ ሲደገስ ክርስቲያኑ ሙስሊሞችን ይጠራል፡፡ ከዛ የሚመጡትን ሙስሊሞች ቁጥር ገምቶ የሚበቃቸውን እንስሳ ያዘጋጃል፡፡ እደ ቁጥራቸው በግ ወይም ወይፈን ይዘጋጅላቸዋል፡፡ ከዛም ሙስሊም እንዲባርክላቸው ይደረጋል፡፡ በቃ እዲህ ነው፡፡” ዛሬ በግ ታርዶላቸው ነው” አለን፡፡ ሙስሊሞችም ሲድሩ ወይም ሲደግሱ እዲሁ ያደርጋሉ፡፡ በጣም ተገረምን፡፡ የጎንደር አማራ አንዱን ዳስ በመጋረጃ ወይም በሸበባ ቅጥል ይከፍልና አንድ ላይ ደግሶ ይዳዳራል፡፡ ሙስሊሞች በዛ በኩል ክርስቲያኖች በዚህ በኩል ጉድ ጉድ እያሉ ሰርጋቸውን ሲያደርጉ በአይኔ በብረቱ አይቻለሁ፡፡ ይህንን ያየሁና የሰማሁ ሰው ታዲያ አንድ ምግባረ ብልሹ አማራ-ጠል ኦሮሞ ጎንደር ላይ ሙስሊሞች ጫና ይደረግባቸዋል ብሎ ሲያወራ በሚዲያ አይቸ ሰውነቴን ሁሉ አንቀጠቀጠኝ፡፡
……..
ጎንደር እኔ በነበርኩበት ጊዜ ወደ ኋላ እንደቀረች እና ልጆችዋም በቁጭት እንደሚንገበገቡ አውቃለሁ፡፡ በተለይ አንዱ ጓደኛችን አጼ ፋሲል ከሞት ተነስቶ ቢያያት አዝኖ ከተማየን የት ጣላችኋት ብሎ ያለቅስ ነበር እያለ በቁጭት እርር ትክን እያለ ያጫውተን ነበር፡፡ እኔም አብሬ እርር ድብን እላለሁ፡፡ በጣም የሚገርመው ተመርቄ በስራ አለም ቆይቸ በሆነ አጋጣሚ ከስምንት አመት በኋላ ወደ ጎንደር ሄድኩ፡፡ እኔ ትምህርት ስጀምር የተጀመሩ ህንጻዎች ከዛን ያህል አመት በኁዋላም አልተጨረሱም፤ ብዙዎቹ እንደ ጅብራ ተግተረው ሳያቸው የድሮው ጓደኛየ ንግግር ትውስ ብሎኝ አልቅስ አልቅስ አለኝ፡፡ አወ ጎንደር ሆነ ተብሎ የተበደለች ከተማ እንደሆነች ግልጽ ነው፡፡ በውጭ አገር የሚገኙ ነዋሪዎችዋ እናልማት ብለው ባርጤዛው ወያኔ አይቻልም እንዳላቸው ሰምቻለሁ፡፡ በርግጥ ወደ ወያኔ ካዝና የሚገባው ከውጭ አገር የሚላክ ገንዘብ በዋናነት ብዙው የአማራ በተለይ ደግሞ የጎንደር እንደሚያመዝን ይታወቃል፡፡ ያ ገንዘብ ብቻውን ጎንደርን እንኳን ከሌሎች ከተሞች ጋር እኩል ማድረግ ይቅርና ከሁሉ የምትበልጥ ትልቅ ከተማ ባደረጋት ነበር፡፡ ከሁለት አመት በፊት ሰሊጥ ብቻ 26 ቢሊዮን ብር እደተመረተ አውቃለሁ፡፡ ግን ነገሩ ሲያስቡት ራስ ምታት ይቀሰቅሳል፡፡ አንድ የምጣኔ ሀብት ባለሞያ ጓደኛየ እደሚነግረኝ የጎንደር ሀብት በሰላም ተሳክቶልን የአማራን መነግስት ብንመሰርት ብቻውን ቀጥ አድርጎ እንደሚይዘው ነው፡፡ ይህ ጓደኛየ “የሸዋና የወሎ ሰው ሩቅ ስለሆነ የጎንደርን ሀብታምነት አያውቅም፤ ቢያውቅ ግን ደስ ይለኝ ነበር” በማለት ይቆጫል፡፡ እኔም በብዙ መልኩ ለመታዘብ እንደቻልኩት ጎንደር ሀብታምና አምራች አገር ነው፡፡ ግን የምርቱ ባለቤት አይደለም፡፡ እያመረተ ያመረተውን እንዳይቀምስ የተደረገ ህዝብ ነው፡፡
……
ጎንደር ላይ በቆይታየ ያየሁትን እና የኖርኩበትን ህይወት ጽፌ አልጨርሰውም፡፡ ይሁንና ለማስታወሻ ብቻ ይህንን አልኩ፡፡ ብቻ ባጭሩ ጎንደር የተማርኩብሽ ብየ ልሰናበት፡፡ የተማርኩብሽ የእምነት አገር መሆንዋን እና ምህረት የተደረገልን እዛ ነው ብየ እፈታዋለሁ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን የቀሰምኩብሽ እላታለሁ፡፡ የሰው ፍቅርን፤ ጨዋታና ደግነትን የተማርኩብሽ እላታለሁ፡፡ ለበጎነትዋ ከሰሜን በኩል የተከፈላትን የአፈርና ጠጠር ክፍያ ሳስብ አማራ ከእንግዲህ ለራሱ ማሰብና አቅጣጫ መቀየር እንዳለበት ጎንደር ምሳሌ ናት ብየ የተማርኩባት ናት እላታለሁ፡፡ የተማርኩብሽ ጎንደር! የተማርኩባት ጎንደር! አማራ ደጋግሞ የተነሳባትና የወደቀባት ጎንደር! የታላላቆቹ ጀግኖች ቅድመ አያቶቻን ምድር ጎንደር! የአማራነታችን ፈርጥ ጎንደር! ዘውድና ክብራችን ጎንደር! ድፍረትና ጀግንነትን ልባችን ውስጥ ያተሙት ያለፉት ጀግኖች አማሮች ምድር ጎንደር! ከፈጣሪ በቀር ሰው የማይፈሩት ጀግኖር አባቶቻችን አገር ጎንደር! ጎንደር ቤተ አማራችን! ስላንች ባሰብን ቁጥር ትልቅነታችን ትዝ ይለናል!
የተማርኩብሽ ጎንደር! የተማርኩባት ጎንደር
መለክ ሐራ ከቤተ አማራ
ጎንደር ቤተ አማራ