Bete Amhara

Bete Amhara

Monday, July 13, 2015

የአማራ ተረት የጥበባችንና የእኛነታችን መስታወት

የአማራ ተረት የጥበባችንና የእኛነታችን መስታወት

ተረት የማህበረሰብ እድገት ደረጃን ይለካል፡፡ ተረት ከጠቅላላ የሰው ልጅ ቋንቋ ውስጥ አንዱ ክፍል ነው፡፡ ባህሉ ያደገ ማህበረሰብ ብዙ አይነትና የተለያየ ጥልቀትና ይዘት ያላቸው ተረቶች ይፈጥራል፡፡ ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ የሚነገሩ ተረቶችን የያዘ ማህበረሰብ ስናገኝ በዛ ተረት ውስጥ ያ ማህበረሰብ ያለፈባቸውን ውጣ ውረዶች፤ እንደማህበረሰብ የኖረባቸውን ዘመናት ርቀት፤ ከሌሎች የሩቅና የቅርብ ህዝቦች ጋር ያለውን ግንኙነት፤ እርስ በእርስ በልዩ ልዩ ዘርፎች ያለውን መስተጋብር፤ የእምነትና ባህል እድገቱን፤ የጦርነት ታሪኩን፤ የንግድና ልውውጥ እድገቱን፤ የምጣኔ ሀብታዊ ስምሪቱን እና እድገቱን….እንማራለን፡፡ የአንድን ህዝብ ያለፈ እድገት እና ያለፈው እድገቱ ለአሁኑ ጊዜ አኗኗሩ ያለውን መሰረትነት ለማወቅ መጀመሪያ ተረትና ስነቃሉን፤ ቅኔና ግጥሙን፤ ፈሊጥና ስላቁን ማወቅ ያሻል፡፡ የተለያዩት ህዝባዊ ተቋማት እያደጉና እየተስፋፉ በሄዱ ቁጥር የህዝቡ ተረት እየበዛ እና እየረቀቀ ይመጣል፡፡ ለምሳሌ የኢኮኖሚ እድገት ቋንቋውን ይለውጠዋል፡፡ የእምነት ተቋማት መደርጀት ተረትን ይቀይረዋል፡፡ ፖለቲካዊ አድማሱ በሰፋ ቁጥር ተረቱ እየሰፋ እና እየጠለቀ ይሄዳል፡፡ ወታደራዊ ድሉ እየተበራከተ በሄደ ቁጥር ተረቱ እየሰፋና እየረቀቀ፤ እየጠለቀ ይሄዳል፡፡ ለምሳሌ ወደግብርና ደረጃ የተሸጋገረ ህዝብ ተረቱ ከግብራና ጋር ይያያዛል፡፡ በዘላንነት የተወሰነ ህዝብ ተረቱ ዘላንነት ይሆናል፡፡ እርስ በእርሱ ሲናጭ የኖረ ህዝብ ተረቱ ስለመናጨት ይሆናል፡፡ ባጭር አገላለጽ ተረት የአንድ ህዝብ ሁለንተናዊ የማህበረሰባዊ እድገት ደረጃ ነጸብራቅ ነው፡፡ ተረቱን በማጥናት የህዝቡን ያለፈና የአሁን እድገቱን በትክክል መረዳት እና ከሌሎች ጋር ማወዳደር ይቻላል፡፡ ህዝብ ሲያድግ ተረቱም አብሮ ያድጋል፡፡

አረቦች በተረት የታወቁ ናቸው፡፡ ምክንያቱ የአሁኑ የአረብ ህዝ በአብዛኛው የባቢሎንና ሱሜሪያን ስልጣኔ ወራሽ ስለሆነ ነው፡፡ በሰው ልጅ ታሪክም ቀድሞ የሰለጠነው አረቡ ክፍል ነበር፡፡ ከዛ የተነሳ የዳበረ ባህል አለው፡፡ የዛ የዳበረ የህዝብ ባህል ክፍል የሆነውም አረቦችን ታዋቂ የተረት ባለቤቶች አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም አካሄድ ተረት የእድገት ምልክት ነው እንላለን፡፡ ምክንያቱም አንድ ህዝብ በተረትና ምሳሌ ነገሮችን የሚወክለውና የሚገልጸው በደረሰባቸው እድገቶችና በሚያውቃቸው ነባራዊ እውነቶች ላይ ተመስርቶ ነው፡፡

ወደአማራ ስንመጣ ሁኔታውን ተመሳሳይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለረጅም ዘመናት በአማራነት ባመዛኙ አንድ አይነት ቦታ እና በተመሳሳይ የአየር ንብረት ክልል እንዲሁም በተመሳሳይ የምጣኔ ሀብታዊ ስራ ተሰማርቶ ስለኖረ ይህንን የሚገልጽ ልዩ ተረትና ምሳሌ አዳብሯል፡፡ የአማራ ተረቶች ስፋት እና ጥልቀት የማህበረሰቡን ዘርፈ ብዙ ያለፉ ስልጣኔዎች የሚያሳዩ ናቸው፡፡ የዛ ያለፈው የማህበረሰብ እድገት ውጤትም ዛሬ በእያንዳንዳችን ህይወት ውስጥ ይንጸባረቃል፡፡ አማራ ትልቅ እድገት ላይ በመድረሱ ምክንያት በአይነታቸው የተለያዩ እና በይዘታቸው አያሌ የሆኑ ተረትና ምሳሌዎች ባለቤት ሆኗል፡፡ ተረትና ምሳሌዎቹን በጥንቃቄ ለተገነዘባቸው ስለ ህዝቡ የሚናገሩት ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ ተረትና ምሳሌዎቻችን የተሳተፍነባቸውን አውደ ውጊዎችን፤ ታሪካዊ ዳራዎችን፤ የእምነት ሁኔታዎችን፤ የንግድ ነገሮችን፤ የአኗኗር ዘይቤዎችን፤ የፖለቲካ ስርአተቶችን፤ የህግ ስሪቶችን፤ የሰው ለሰው ግንኙነት ደንቦችን፤ መንግስታዊ ህግጋት እና ደንቦችን ሰማያዊ እና መድራዊ ህይዎቶችን….በተገቢው መንገድ ይገልጻሉ፡፡ የአማራን ተረቶችን ብቻ በአጽንኦት በመገንዘብ የህዝቡን ያለፉ የእድገት ደረጃዎች እና አኗኗር ዘይቤዎችን በቅጡ መረዳት ይቻላል፡፡ ሰፊ እድገት ሰፊ ተረት፤ ጥልቅ ፍልስፍና ጥልቅ ተረትን ይወልዳል፡፡ የአማራ ተረትና ምሳሌዎች በጣም ረቂቅ ከመሆናቸው የተነሳ አንዱ ብቻውን ብዙ ነገር መግለጽ ይችላል፡፡ በአጭር ቃላት ስንትና ስንት ነገርን በቀላሉ መግለጽ የነጠረ ተረትና ምሳሌ ባለቤትነትን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ደግሞም ተረቶች ፍልስፍናዊ ባህርያት አሏቸው፡፡ ያለፈው የአማራ ህዝብ የደረሰበትን የአስተሳሰብ እና የፍልስፍና ደረጃ ለማወቅ የተረቶችን ይዘትና ስፋት ማወቅ ብቻውን በቂ ነው፡፡

አንድ ህዝብ በጣም ሲያድግ ቁሳዊ ነገሮችን ከምናባዊ ነገሮች ጋር በማቆራኘት ምጡቅ የሆነ ፍልስፍናዊ ተረትና ምሳሌ ይፈጥራል፡፡ ቁስና ምናብን አንድ ላይ አጣምሮ ረቂቅ ትርጉም እንዲኖራቸው ማድረግ የህዝብን የረጅም ጊዜ የባህል እና ስነ አእምሮአዊ እድገት የሚመለክት ነው፡፡ ያላደጉ ህዝቦች እምብዛም የመንፈስና የቁስ ረቂቅነትን መግለጽ የሚያስችል ተረትና መሰል የቋንቋ ሀብት ይጎድላቸዋል፡፡ እያደጉ ሲሄዱ ግን ተረትና ምሳሌያቸውም አብሮ ያድጋል፡፡ የአማራ ተረትና ምሳሌዎች ታዲያ ቁሳዊውን አለም ከምናባዊው አለም ጋር በማጣመር ረቂቅ የሆነ ትርጓሜን የሚሰጡ ናቸው፡፡ የተረትና ምሳሌዎቹ ባህርያትም የህዝቡን ያለፈና የአሁን የእድገት ደረጃ ያመለክታሉ፡፡ ባጭሩ አንድ ህዝብ ሲያድግ ሰፊ ቋንቋ ይኖረዋል፡፡ ያ ሰፊ ቋንቋ ብዙ ቁሳዊና ምናባዊ እሴቶችን እና ነባራዊ ሁነቶችን ለመሰየም ይረዳል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ሰፊና ጥልቅ ተረትና ምሳሌ ይፈጠራል፡፡

ፍላጎትና ስሜትን በምሳሌ ማስረዳት መቻል የስነልቡና እድገትና ባህርይንም ያመለክታል፡፡ የውስጥን ፍላጎትና መሻት በምሳሌ አድርጎ መናገር እና ለሰሚው የምርምር ጊዜና እድል በመስጠት ማሳካት የሚችል ህዝብ በጣም ለረጅም ጊዜ በአንድነት ኖሯል፤ ስለዚህም በውጫዊ ንግግር ብቻ ሳይሆን በውስጣዊ ፍላጎትም ይተዋወቃል ማለት ነው፡፡ የአማራ ተረትና ምሳሌዎችም የሚያሳዩት ይህንን ነው፡፡ በተረትና ምሳሌዎች የአንዱን ወገን ውስጣዊ ፍላጎት ማወቅ የሚያስችል ጥበብ፡፡ እናም እነዚህን ተረትና ምሳሌዎቻችንን ያለፈው ትውልድ ሳይንሳዊ ምርምር ውጤት እላቸዋለሁ፡፡ ለምን ቢባል የሚያስተላልፉት መልእክት እና ለአነጋገር ቀላል መሆናቸው ትልቅ የጥበብ ውጤት መሆናቸውን ያሳያልና፡፡ የተረትና ምሳሌዎች ረቂቅነት ረቂቅ ትውልድ እንደነበረ ያመለክታል፡፡ ይህም ያ ረቂቅ ትውልድ የበለጸገ ባህል እንደነበረው ያስረዳናል፡፡ ለትክክለኛ ነገሮች ትክክለኛ የተረትና ምሳሌ ጥምረት መፍጠር በራሱ የህዝቡን ጥበብ የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድም አማራ የተረት ባለሀብት፤ ባለቤት ነው እንላለን፡፡

ታዲያ ስለምንድር ነው በአማራ ላይ ላፉት 24 አመታት ከፍተኛ የተረትና ምሳሌ ማጥላላት ዘመቻ የተደረገበት ብለን ስንጠይቅ የአማራ ጠላቶች የተረትና ምሳሌያችንን ሀይል እና ያለፈውን የህዝባችንን ዘርፈ ብዙ እድገት የሚያረጋግጡ በመሆናቸው ከክፉ ቅናት የተነሳ ነው ብለን እንደመድማለን፡፡ ተረታችን ላይ የተዘመተበት ምክንያትም እንቁ በመሆኑ ነው፡፡ ድንጋይ የሚወረወረው ፍሬ ወዳለው ዛፍ ነው እንዲሉ ተረትና ምሳሌያችን ጠላቶቻን ሊያሟርቱበት እንደከጀሉት ሳይሆን የሆነ እንቁ ነገር መሆኑ ነው፡፡ አማራን እና የአማራ የሆነውን ሁሉ ማጥፋት በሚለው አጀንዳ ስር ዋነኛ ሰለባ የሆነው ተረትና ምሳሌያችን ነው፡፡ ድንቅ ሀብታችን ባይሆን ማን ይነካው ነበር! የሚገርመው ተረታችን የተዘበተበት በራሱ በአማርኛ ተረት ነው፡፡ ነጋ ጠባ ተረት ምናምን እያለ የአማራን ባህል ሊያንቋሽሽ ሲዳክር የነበረው የወያኔው አምበል አገሪቱን በተረት ብቻ እንደ“መራት” የሚታወስ ነው፡፡ ተረታችንን በተረታችን ለማጥፋት ብዙ የጣረ ነው፡፡

ወዳጀቸ ካሉን ሀብቶች ሁሉ ትልቁና ዋነኛው ተረትና ምሳሌያችን ነው፡፡ ያለፈው ትውልድ ሊነበብ የሚችለው በቀዳሚነት በተረታችን ውስጥ ነው፡፡ እኛነታችን በተረታችን ታትሟል፡፡ ተረቴ እወድሀለሁ፡፡ ተረቴ የአባትና እናቶቸ ጥበብ፡፡ እኔም ለልጀ አስተላልፍሀለሁ፡፡

ድል ለአማራ
መለክ ሐራ ከቤተ አማራ