Bete Amhara

Bete Amhara

Monday, July 13, 2015

ሃረግ

ሃረግ
ፍልቅልቅ ፣ቀይ ፣የደም ገንቦ ናት ። እንኳን ሳቋ ውሽክታዋ ልብን ያርዳል።አይነ ኮሎ ናት።ደም የቋጠሩ የመሰሉ ከበድ ያሉት ከናፍርቶቿ ልክ እንደ እንቦቀቅላ ህፃን ከንፈር ይርበተበታሉ ። ቁመቷ ልከኛ ነው ። መቃው አንገቷ ላይ አረንጓዴ የመሰሉ የደም ስሮቿ የአንገት ፎጣዋ ሊሸፍናቸው ስላልቻለ ደሟን ይዘው ሲሯሯጡ ፍንትው ብለው ይታያሉ። ዳሌዋን የሚያገማሽር ጠበቅ ያለ ጥቁር ጅንስ አድርጋለች ።ሰፋ ያለው ቡላ ሹራቧ ወገቧን እንደ ፅዋ ሙዳይ አልብሶታል። ችቦ አይሞላ ወገቧ በሹራቡ ቀዳዳ እንደ ዘንዶ ሲጥመለመል ይታያል። የሹራቧን እጅጌ ሰብሰብ አድርጋዋለች። ልክ የአንገቷ አይነት አረንጓዴ መሰል የደም ስር ክንዷ ላይ ተጋድሟል። እሱን ተከትዬ ስሄድ አይኖቼ አለንጋ እጣቶቿ ላይ ደረሱ። የጥፍር ቀለሙ ብናኝ ተጣብቆባቸው የሚብረቀረቁ አለንጋ እጣቶች… …
አይኖቼን አሸት አሸት ፣ጭፍን ክፍት አደረኳቸው … ያየሁትን ውበት ይበልጥ አጉልተው አሳዩኝ ።ህልም አለመሆኑንንም አወቅኩ ። የማየው ነገር እውነት ነው። ከአሁን በፊት አይቼው የማላውቀው ውበት እንደ ጭስ አባይ ፏፏቴ ከፊት ለፊቴ ይንፏፏል። ጠረኗ አፍንጫዬን ስቦ አንገቷ ስር ሊያጣብቀው ትንሽ ቀረው። "በስመ አብ" ለማለት አጉተመተምኩ። ሰማችኝ መሰል ዞርርር ስትል ከነፈገግታዋ አይን ከአይ ግጥምምም ። ድምፅ አውጥቼ "በስመ አብ!" አልኩ እና አንገቴን ሰበር አደረኩት ። ለካ እንዲህ አይነት ሴት ታስፈራለች! የውበት መብረቅ መታኝ ። ክው ብዬ ቀረሁ።
ከደባርቅ ወደ ጎንደር የሚሄድ አውቶብስ ለማሳፈር ግፊያ ላይ ነው ያዬኋት ። ከሚያስጠሉኝ ነገሮች አንዱ ግፍያ ነው። እሷም እንደኔ ግፊያው አስጠልቷት ይሁን አቅም አጥታ ከኋላ ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ሁና ቁማለች ። እኔ ከሷ በኋላ የመጨረሻው ሰው ነኝ። የምጋፋበት ጉልበት አጥቼ አይደለም ። ግን ለሆነ ነገር ከተጋፋው እራስ ወዳድ የሆንኩ እየመሰለኝ አፍራለሁ ፣አልጋፋም። ወላ ቁሜ ልሂድ እንጂ አልጋፋም።
"አቦ አንተም ተጓዥ ነህ? አቦ በናትህ ከሆንክ እንደምንም ብለህ ቦታ ያዝልኝ ፣ በእግሬ ብዙ ርቀት ተጉዤ ነው እዚህ የደረስኩት ቁሜ መሄድ አልችልም ። ውልቅልቅ ብያለሁ… …እ" …አላስጨረስኳትም ።ፈንቅል ፣ ሰንጥቅ ክፍለ ጦር ሆንኩ። ማን ከፊቴ ይቁም? ብቻ ከፊቴ መቦጫጨር ስሜት እና ከትክሻዬ መዘንጠፍ ስሜት ጋር ሆኜ እራሴን ባለሁለት ወንበር ባለቤት ሆኖ አገኘሁት። በመስኮት አንገቴን አውጥቼ ግዳዩ እንደሰመረ አበሰርኩላት ። ፍልቅልቅልቅ… እያለች ነው። "አቦ ተፈልቅለቂ! " አልኩ በሆዴ …
ዳባት ሳንደርስ የእሷን እና የቤተሰቧን ታሪክ አውርታኝ ፣ የእኔ እና የቤተሰቤን ታሪክ አውርቻት ጨርሰናል። በሂዎቴ በቀላሉ የተግባባሁት ታሪኬን በአጭር ሰአት የዘረገፍኩለት ሰው አንደኛዋ እሷ ናት ። ርግብ ነገር ነች ። የምትታመን፣ ሳትናገር እንዲንከባከቧት የምታስገድድ ፣ፊቷን ቢነኩት የሚቆሽሽ የምትመስል መልአክ ነገር ።
ሃረር አራተኛ የሚባል ሰፈር ነው ተውልዳ ያደገችው። እናቷ የመንዝ አባቷ ደግሞ የጎጃም አማሮች ናቸው።አባቷ የደርግ ወታደር ሻለቃ ነበር ። በሂዎት የለም ። ሽሬ ላይ በተካሄደው ጦርነት የህወሓት የእጅ ቦንብ በጣጥሶታል። ለአስከሬንነት እንኳ አልበቃም። እናቷ በአንድ የመንግስት ድርጅት ውስጥ ፅዳተኛ ነች ። በምታገኛት ኩርማን ደሞዝ እሷን እና ሌሎች ታናናሽ ሁለት እህቶቿን ታስዳድራለች። እቁብ ገብታ ይችን የውበት ገንቦ ልጇን ሃረር መምህራን ኮሌጅ በዲፕሎማ አስመረቀች።
ቶሎ ተመርቃ ወጥታ ስራ ይዛ ሁለት ታናናሾቿን የማስተማር ህልሟ ከሰመ ። ሃረሪ ክለል ውስጥ አማራ ሆኖ መገኘት ስራ በቀላሉ አያስገኝም። ጎረቤት ክልል ኦሮምያም ለአማራዋ ስራ የለውም። በሱማሌዎች የሚሾረው ድሬድዋ መስተዳድርም ስራ አላገኘላትም።የሚገርመው ኦሮምኛ በደንብ ሃደሪኛ ትንሽ ትንሽ ትችላለች። ስራ ግን ጠፋ ። መከራ አየች ።ወጣች ወረደች… ሃባ ነገር የለም ። በመጨረሻም እሷ እና መሰል አማሮች" አማራ ክልል ሄዳችሁ ስራ ፈልጉ" ተብለው ቁርጣቸው ተነገራቸው።
"ገላዬን ለወሲብ ቄራ ከማቀርብ አቦ !ልሂድ እና ልሞክር ብዬ ባህርዳር መጣሁ ። የማላውቀውን የአባቴን ሃገር ረገጥኩ ፣ የሆነ የማላውቀው ስሜት ወረረኝ ።አባቴ በቅጡ ቤተሰቦቹን እንኳ ሳያስተዋውቀን፣ ሃገሬን ኢትዬጵያ እንዳለ ነው ወጦ የቀረ። ባህርዳር ስደርስ የምተዋወቀውን ሰው ሁሉ ስለ አባቴ እጠይቅ ፣ፎቶውንም አሳይ ነበር ። የሚያውቀው ሰው አንድም አላገኘሁ። መድሃኒያለምን እንደ እኔ አይነት ሞኝ እኮ የለም። አቦ ሁሉም ሰው ዘመዴ ይመስለኛል። አሁንም እንደዛ ነው ሚሰማኝ…በአማራነቴ ስለተገፋሁበት አማራ ሁሉ ዘመዴ ነው ሚመስለኝ ። ሁሉንም እየያዝኩ ባቅፋቸው እወዳለሁ። ……ያው የአማራ ትምህርት ቢሮ የበየዳ ትምህርት ቤት አስተማሪ አደርጎ ቀጠረኝ። ምንም አማራጭ የለኝም። ትራንስፖርት አስቸጋሪ ነው። ብዙ ግዜ አይገኝም ከተገኘም የጭነት መኪና ላይ እንደ ጆንያ ሁነህ ነው ። አንዳንዴ መኪና ጭቃ ይያዛል ፣ ገደል ይናድ እና መንገድ ይዘጋል አንዳንዴም መገልበጥ አለ። ያው ደባርቅ ለመድረስ በግርህ ከ40 እስከ ስልሳ ኪሎሜትር ልትጓዝ ትችላለህ። አማራነት ከሃረር አስባርሮ ራስ ደጀን ጣራ ላይ ሰቀለን። አቦ ግን ምን አድርገን ነው?…ከደባርቅ ጎንደር ፣ ከጎንደር አዲስ አበባ ከአዲስ አበባ ሃረር እጓዛለሁ። የእንጀራ ነገር ……………"
ቅድም በውበቷ አሁን በታሪኳ አንገቴን አቀረቀርኩ ። ውስጤ ተላወሰ ፣ እንባዬ ሳላውቀው እዬፈሰሰ ነው ። ወደ መስኮት ዞርኩ እና እንባዬን በመዳፌ አበስኩ ። "አቦ ተዋ እኔ ለምጀዋለሁ ። ከህዝቤ መሃል እንዳለሁ ነው ሚሰማኝ። ሰላም አለኝ ። እውነቱን ልንገርህ አይደል። አሁን አሁን እንዴውም ወደ ሃረር ስሄድ ነው የሚከፋኝ። የእናቴ እና የእህቶቸ ነገር ሆኖብኝ እንጂ አቦ እዚህ ነው መኖር የምፈልገው። " ፈግግታዋ ውስጥ ፍፁም እውነተኝነት አለ ። አየሁት።
መጀመሪያ ላይ ሳያት የወንድነት ስሜት ነበረኝ አሁን ግን የወንድምነት ስሜት ሞላብኝ ። እቅፍ አደረኳት ። ታቀፈችኝ። ………ጎንደር ስንደርስ እኛ ቤት አድራ እንድትሄድ ጠየኳት ። ደንቢያ ውስጥ ከጯሂት አካባቢ የሚመጡ አንዲት ሴት እና አንድ ወንድ የሃረር ጓደኞቿ (እንደሷው በአማራነት የተገፉ መምህሮች ናቸው ። )አዘዞ እየጠበቋት እንደሆን ነግራኝ ተሰናብታኝ ሄደች ። እኔም አንገቴን እንዳቀረቀርኩ በመከፋት ስሜት ሁኜ ፋሲል ሆቴል ላይ ወርጄ የራስ ሚካኤል ስሁልን ቤተ መንግስት በቀኝ አይኔ በጎሪጥ አሻግሬ እያዬሁ የአስተዳደር ደረጃውን ቀስ እያልኩ ወጣሁ እና ወደ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ሰፈር አቀናሁ… …
በሚቀጥለው አመት ጎጃም ሃገረ ሰላም አካባቢ እንደተመደበች በስልክ ነገረችኝ ።ኢትዬጵያን ለቅቄ እስክወጣ ድረስ አልፎ አልፎ ስልክ እንደዋወል ነበር ። ከወጣሁ በኋላ ግን ስደውልላት ስልኳ አይሰራም። ደጋግሜ ሞከርኩ አይሰራም ። ከሆነ ግዜ በኋላ ስልኳም ጠፋብኝ።አሁን የት እንዳለች አላውቅም ። ፌስቡክ ላይም ፈለኳት አላገኘኋትም ። የምስራቋ የውበት ኮከብ በዘረኝነት ጥልመት የት ተሸብባ ይሆን? … ……
መሳፍንት ዘ አማራ