Bete Amhara

Bete Amhara

Wednesday, July 8, 2015

ከዙሉ ወደ ዙሉ የኢትዮጵያዊያን እጣ ፋንታ

ከዙሉ ወደ ዙሉ የኢትዮጵያዊያን እጣ ፋንታ
እንደ ኢትዮጵያዊ ሆኘ ሳስበው በመላው ዘጎች ላይ የሚደርሰው በየአገሩ መገደል ያንገበግበኛል፡፡ ከዛም በላይ ተበቃይ የሌለው ህዝብ መሆኑን ሳስብ ልቤ ይደማል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በሳኡዲ አረቢያ ሲታረዱ አንብቻለሁ፡፡ በሊብያ፤ በግብጽና በሱዳን መከራ ሲደርስባቸው አዝኛለሁ፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጓዙ በሚያገኛቸው መከራ አዝኛለሁ፡፡ በየመንና በጅቡቲ እንዲሁም በቀይ ባህር የአሳ ራት ሲሆኑ በእልህ ተንገብግቤያለሁ፤ በተለይም አንድ ውርጋጥ “የአሶች ጸሎት ምላሽ አገኘ” ብሎ ሲጽፍ የምሆነውን ሁሉ ማጣቴን አስታውሳለሁ፡፡ ከዚህ ሁሉ በባሰ ሞራሌ ተነክቶ ወያኔንም ደም ስሬ ጠልቆ እስኪገባ ድረስ ጠልቸው የቀረሁት በዚህ ሁሉ ችግር አንድም ቀን እንኳ ዜጎቸ ብሎ ምንም ነገር ባለማድረጉ ነው፡፡ ከግዴለሽነት አልፎም የተሳለቀበት ጊዜ በመኖሩ ነው፡፡ ለምሳሌ አጼ መለስ በሊብያ ስለሚሰቃዩ ወገኖች ሲጠየቅ ሲሄዱ በእግራቸው ነው የሄዱት፤ በሄዱበት እግራቸው መመለስ ይችላሉ ብሎ የተሳለቀውን እስከዛሬ አልረሳውም፡፡ አሁንም በቁሙ በተቃጠለ ሰው ቁጥር እየተከራከሩ ይገኛሉ፡፡ ልብ በሉ፡- እነሱ ሞተ አልሞተም ሳይሆን ክርክራቸው ቁጥር ላይ ነው፡፡ በእነሱ ቤት ሰውም ከቁጥር የዘለለ ዋጋ የለውም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት አንድና አንድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ መንግስት ስለሌላት፤ እየተገዛች ያለቸው በጠላት እጅ ስለሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያን፤ ባንዴራዋን፤ ታሪክና ባህሏን፤ ኢትዮጵያዊያንን ተዋግቶ እያደማት እርሱም እየደማ ነው የመጣው፡፡ የተዋጋው ኢትዮጵያዊነት ከተባለ መንፈስ ጋር ነው፡፡ ሲነሳ ከኢትዮጵያ ጋር ተጣልቶ፤ ከታሪኳና ሁለንተናዋ ጋር ተኳርፎ ነው፡፡ ይህችን አጥንቱ ስር ድረስ ጠልቆ በገባበት ጥላቻ የተዋጋትን አገር መናፍስትም ተባበሩት መሰል እጁ ላይ ጣላት፡፡ የሸሻትን፤ የተዋጋትን አገር፤ ሊያጠፋት የተነሳትን አገር ድንገት በክፉ አጋጣሚ እጁ ላይ ወድቃ አገኛት፡፡ እናም በልቡ የነበረውን ሁሉ ቂም ሁሉ እየተበቀላት ይገኛል፡፡ ይህ ቡድን ሲጸነስ በኢትዮጵያ ጥላቻ ማህጸን ውስጥ ነው፡፡ ሲረገዝም በኢትዮጵያ ጥላቻ ሆድ ውስጥ ነው፡፡ ሲወለድም ከኢትዮጵያ ጥላቻ እናት ነው፡፡ በጠቅላላው በጥላቻ ተጸንሶ፤ በጥላቻ ተረግዞ፤ በጥላቻ የተወለደ፤ በጥላቻ የጎለመሰ እና እስከጥላቻው እያረጀ ያለ ቡድን ነው፡፡ የጠላት ህዝብ ገዥ በመሆኑ መቸም ሊራራ እና ፍቅር ሊሰማው አይችልም፡፡ የዚህ ሁሉ ቸልታ ምንጩ የሚገዛትን አገር እንደ አገሩ ካለመቁጠር እና የሚገዛውን ህዝብ እንደ ህዝቡ ካለመመልከት የመጣ ነው፡፡ በተጻራሪው ራሱ ገድሎ አልጨርስ ያለውን ህዝብ በሌላ ወገን ሲገደልለት ጮቤ ይረግጣል፡፡ እና ኢትዮጵያዊያን ሆይ ለሩቁ ዙሉ አሳልፎ የሰጣችሁ የቤታችሁ ዙሉ ነው፡፡ የቤታችን ዙሉ ከጎረቤታችን ዙሉ የከፋ ነው፡፡ የራሳችን ዙሉ በህይወት እስካለ ድረስ ገና ብዙ ክፉ እናያለን፡፡ በዙሉ ክፉ መዳፍ ስር እስካለን ድረስ ገና የኛ ነገር ከአንዱ ዙሉ ወደ ሌላው ዙሉ በቅብብሎሽ ማለቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን አንጀት የሚበላ ህዝብ ነው፡፡ መላ ህይወቱ ከዙሉ ወደ ዙሉ ነው፡፡ ከድጡ ወደማጡ እንዲሉ፡፡ በቤታችን ዙሉ የምትበሉም ሆነ በጎረቤት ዙሉ የምትቃጠሉ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ መጽናናትን እመኝላችኋለሁ፡፡
መለክ ሀራ ከቤተ አማራ