እንኳን ዮሐንስ ምኒልክ ተሰድቧል!
_______________________
_______________________
ክቡር ሀዲስ አለማየሁ ወንጀለኛው ዳኛ ላይ እንዲህ ይለሉ፡ “ብዙ ሰው የተናገረው ውሸት እውነት ይሆናል”፡፡ ሌላም አባባል አለ-- ሀብታም ቢዘላብድ እውነት የተናገረ ይመስለዋል የሚል፡፡ ከሳሽ የተከሳሽን መልስ ቢያውቅ ከቤቱ አይወጣም ነበርም ይባላል፡፡ ብዙ ጊዜ የአባባ አጼ ምኒልክ ስም በከንቱ መነሳት ሲያንገበግበኝ ነው የኖርኩት፡፡ ሳልበቀልላቸው በመቅረቴ አጸደ ነፍሳቸውን ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ በበኩሌ ምኒልክን እጅግ በጣም እወዳቸዋለሁ፡፡ ለአምልኮት ትንሽ የቀረው ፍቅር ነው ያለኝ ለእሳቸው፡፡ ምኒልክ ባያደርጉት ብለህ የምታስበው ምንድነው ብባል ግን ከተከዜ ማዶ ተሻግረው ጦርነት ማድረግ አልነበረባቸውም ነው የምለው፡፡ እርሳቸው በሞት ሽረት ትግል ያተረፉት ሀገር ልጆች ናቸው ዛሬ የምኒልክ ቀንደኛ ጠላቶች፡፡ ብዙ ጊዜ የሚሉት “ምኒልክ ትግሬን ለማዳከም ነው መረብ ወዲያ ማዶ ያለውን ግዛት የሰጠው፡፡” እውነቱ ግን በዛ ጊዜ ምንም ያልነበረውና ጨርሶ የተንኮታኮተ አካባቢ ነበር፡፡ ምኒልክ ለያይቶናል ካሉ ደግሞ በ1983 አንድ መሆን አይችሉም ነበር? ለነገሩ አማራ አንድ አድርጎ ያኖረውን አገር ኤርትራና ኢትዮጵያ ብለው ለሁለት ተካፍለው እንኳ ማስተዳደር አቅቷቸዋል!
ታዲያ እኛ ስለራሳችን ስንናገር አላስወራ እያሉ አስቸገሩን፡፡ እምቢ ብለው ከመጡ እንግዲህ ምን እናደርጋለን መንገር ነው እንጅ፡፡ ምኒልክ ትግራይን አድነዋል፡፡ ያ ግን እንደክፉ ነገር ነው የተወሰደባቸው፡፡ ምኒልክ ሲዋጉት የኖሩት ጦርነት የመጣው በዮሐንስ መሆኑን እንኳ መናገር አይፈልጉም፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝ ይሄን ሶስተኛ ክፍል ተማሪ የሚገነዘበው ታሪክ እዚህ በማምጣቴ፡፡ ምን ይደረግ እንግዲህ፡፡ አንዳንዴ ወረድ ብሎ ማቅመስ ነው እንጅ፡፡ በተቃራኒው ታዲያ ዮሀንስ ከሱዳን የጸረ ቅኝ ግዛት ሀይሎች ጋር የተዋጋውን ጦርነት እንደጀግንነት ቁጠሩልን ይላሉ፡፡ ኧረ ለጎንደር ብሎ ነው የተዋጋው ሁሉ ይላሉ! እውነቱ ግን ዮሐንስ አለማቀፍ ባንዳ ነበር፡፡ የእሱን ያህል የባንዳነት ታሪክ ያለው ንጉስ ሰምቸ አላውቅም፡፡ በመጀመሪያ እንግሊዞችን እየመራ አምጥቶ ቴዎድሮስን አስገደለ፡፡ከቴዎድሮስ ጋር ባይስማማ እንኳ ድንበሩን መከላከል ይችል ነበር፡፡ ቴዎድሮስ ለምሳሌ በሽፍትነት እያለ የጎንደር ቤተ መንግስት ያሳድደው ነበር፡፡ ነገር ግን ቱርኮች የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው ሲገቡ ገጥሞ ተከላከላቸው፡፡ አልፈው ሄደው የጎንደርን ቤተ መንግስት ይውጉልኝ አላለም፡፡ ዮሐንስ ግን አልፈው ሄደው ንጉሱን ይውጉልኝ ብሎ የሀገር ክህደት ፈጸመ፡፡ በእውነቱ በዚህ ብቻ ስቅላት ይገባው ነበር---አገር በመካዱና ንጉሱን አሳልፎ በመስጠቱ፤ ከአገር ጠላቶች ጋር በማበሩ፡፡
ቀጥሎ ከመሪ የማይጠበቅ የሎሌነት ውል በመዋዋል ዋና ጠላቶቹን አፍንጫው ስር አስቀምጦ አፍሪካዊውን ጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግል የሚያደርገውን የሱዳን ህዝብ ወጋ፡፡ ያንን ያደረገውም ቴዎድሮስን ወግተው እና መሳሪያ አስታጥቀው ንጉስ እንዲሆን ያደረጉትን ጌቶቹን ለማስደሰት ነው፡፡ ይህ የአሸርጋጅነት ባህርይ ነው እስካሁን ዋጋ ሲያስከፍለን የኖረው፡፡ በዚህም ድርጊቱ አገር አቀፍ ባንዳ ብቻ ሳይሆን አለማቀፍ ባንዳ ሆነ፡፡ ኢትዮጵያን ብቻ አይደለም የካዳት፡፡ አፍሪካን ጭምር እንጀ፡፡ አለማቀፍ ባንዳ ነው ስንልም በእፍሪካ እና በኢትዮጵያ ምድር ላይ የተዋዋለው የቱርክን፤ የግብጽን፤ የጣልያንን እና የእንንሊዝን ጥቅም የሚያስጠብቅ ባንዳዊ ውል በመፈራረሙ እና ውሉን ለማስፈጸም ጎጅ እርምጃ በመውሰዱ ነው፡፡ እንግዲህ ወንጀልን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም እንደሚባለው እሱም ባለማወቁ የሰራው ስህተት ከመወቀስ አያድነውም፡፡ አለማወቅ ራሱ ወደሀገር መሪነት ሲመጣ ደግሞ ትልቅ ሀጢአት ነው፡፡ እናም ዮሐንስ አፍሪካ ላይ ባደረሰው በደል የተበሳጩት ሱዳኖች መጥተው ጎንደርን አቃጠሏት፡፡ ዮሐንስ ባይነግስ ጎንደርን ምን ብለው ያቃጥሏት ነበር? የእርሱን ክህደት ለመበቀል ነው ጎንደርን አቃጥለው ህዝቡን አርደውት የሄዱት፡፡ ለዮሀንስ አላዋቂነት ጎንደር ራስዋን ከፈለች እና ፍርስራሽ ሆነች፡፡ ዛሬ እንድትቃጠል ያደረጋትን ጎንደርን ሲጠብቃት እንደሞተ አድርገው ሊያሳምኑን ይሞክራሉ፡፡
ደግሞ የሚገርመኝ የነገስታትና የመኳንንት የፈረስ ስሞች ጀግንነትን የሚገልጹ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ዞብለው፤ አባታጠቅ፤ አባዳኘው… የዝርፊያ ወይም የውንብድና የፈረስ ስም የነበረው ግን ዮሐንስ ብቻ ነበር፡፡ አባ በዝብዝ የሚባል የፈረስ ስም፡፡ መበዝበዝ ከጥንትም ነው እንዴ ነገሩ?
አሁንም አላርፍ ያለ በልኩ መልስ ይሰጠዋል!