Bete Amhara

Bete Amhara

Saturday, July 11, 2015

ስለ አንጾኪያ ገምዛ

ስለ አንጾኪያ ገምዛ 
*****************
ከሲራክ ተራራ ስር- አንጾኪያ...
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሔኖክ ስዮም ዛሬ ደግሞ ወደ አንጾኪያ ይዞን ሄዶ አስገራሚውን የሲራክ ተራራን ያስጎበኘናል፡፡
ሰሙን እንጂ ሀገሩን ለማታዉቁ ወደ ደጉ ምድር እያቀናሁ ነው፡፡ ደግነትን ነፍሱ ብቻ ሳትሆን ምድሩም ከምትሰብከው አንጾኪያ ገምዛ፤ የወረዳ ስም ነው፡፡ አንጾኪያ የሚለውን ቃል ባህር ማዶ ስትፈልጉት ለኖራችሁ፤ እነሆ እኔና አንጾኪያ ከሲራክ ተራራ ስር ተገናኝተናል፡፡
አንጾኪያ የሰሜን ሸዋ ዞን ወረዳ ናት፡፡ አሁን ያለሁት መኮይ ነው፡፡ መኮይ ደስ የሚል አየር ያላት ከተማ፡፡ እንደኔ መምጣት የምትሹ ከሚሴን ረግጣችሁ ከከሚሴ አንጾኪያ መሳፈር ግድ ነው፡፡ አዲስ አበቤዎችን 347 ኪሎ ሜትር ርቃ ያለችዋ ከተማ፤ የገበሬዎች ላብ ውብ ያደረጋት፡፡
የመኮይ አየር ደስ ይላል፡፡ የዳዋ ጨፋና የአርጡማ ፋርሲ ገበሬዎችን ወዝ ንፋስ ያመጣዋል፡፡ የግሼ ራቤል ደመና ዝናብ የሚሆንበት ሰማይ ነው፡፡ የመንዝ ጌራዎች ሀሴት የሚያውዳት፡፡ እንደልቧ ተዘርግታ መገበያየት የምትችል፡፡ ብትጣራ እስከ አልብኮ የምትሰማ፤ ብታዝን ሀዘኗ እስከ ኤፍራታ ግድም የሚጮህ፡፡
መኮይ ሆኜ ገዝፎ የማየው ሲራክ ነው፡፡ ሲራክ ትልቁ ተራራ፡፡ እነ ማጀቴን ቁልቁል የሚታዘብ፡፡ ግሼን ከአንጾኪያ አላስተያይ ያለ፡፡ አምቦ ውሃ ከአንጾኪያ ቀበሌዎች አንዷ ናት፡፡ የረገጣት ሁሌም አይኑን ሲጨፍን ያንን ለም ማሳዋን ሲመለከት ይኖራል፡፡ አምቦ ውሃ የቸርና ለጋስ ገበሬዎች የበረከታቸው ማሳያ ናት፡፡ ማጀቴ ስትደርሱ ጠጇን ከብረት ምጣድ ጥብሷ ጋር ተቋደሱት፡፡
ወደ ጨለማ ዋሻ ልወስዳችሁ ነው፡፡ የት ነን መሰላችሁ? ዋሻ አንገት ቀበሌ፡፡ ድንቁን ዋሻ ፍለጋ ዋሻ ጎጥ፤ ከመኮይ ተነስተን እዚህ ለመድረስ በመኪና እና በእግር 2 ሰዓት ሊፈጅብን ነው፡፡ የእግር መንገዱ ብዙም አይደል፤ እየተጫወቱ በ1፡30 ውስጥ ፉት ይሉታል፡፡
ጨለማ ዋሻ እንደስሙ ነው፡፡ ጨለማ ነው፡፡ ሦስት ተራሮች ከበውት ተደብቆ የኖረ ዋሻ፤ ሶስቱ ተራሮች ግዳሜ፣ ጠይቦ እና ቅኔ ጎራ ናቸው፡፡ ዛሬ ቀላል የሚመስለው ዋሻ ያኔ በክፉ ቀን ከጣሊያን ጥቃት ማምለጫ ምሽግ ነበር፡፡ ዛሬ በደግ ቀን የሚጎበኘው ጠፋ እንጂ፤ ሀገሬው ሞክሮ ያልተሳካለት እልፍ ቅርስ በበርሜል በበርሜል ከዋሻው ሆድ መደበቁን ይተርካል፡፡ ነዋየ ቅድሳት ጭምር የወጣበት ጊዜ ነበር፡፡
ሌሎች የጨለማ ዋሻን ገድል ያሰፉታል፡፡ የጨለማ ዋሻን የደፈረች አንድ ውሻ በዚህ ገብታ አስቴ ጎማ በተባለው አቡዬ ሜዳ ተራራ ወጣች፡፡ ይህ የዋሻውን ርዝመት በወግ ለመቀመር የቀረበ ታሪክ ይሆናል፡፡ ወይም እውነት፤ ባልተጠና ዋሻ ዳር ቆሞ ብዙ ማለት ከማስተዛዘብ ያለፈ ትርፍ የለውም፡፡ አፈጣጠሩ ተአምር መሆኑን ግን ተደመን እንመሰክራለን፡፡
አናቱ ላይ ሆኖ ቆላማውን የሰሜን ሸዋ ምድር በአንድ ፊት፤ ደጋማውን የመንዝ ሀገር በሌላ ገጽ መመልከት ከጨለማ ዋሻ፤ ከሲራክ ግርማ ሞገስ፤ ከመኮይ ደግነት ጋር ቢኮመኩሙት አይጠግቡትም፡፡
ግን ልምከራችሁ እዚህ ደርሳችሁ አትመለሱ፡፡ አጥቆ ቀበሌ ብላችሁ ፈልጓት፤ ድካም የሚያስለቅቅ ተፈጥሮን የታደለች ስፍራ ናት፡፡ እዚያ ስትደርሱ ገዳም ጊዮርጊስ አለ፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአጼ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግስት የተገደመ ድንቅ ገዳም፤ ተራራማ ስፍራ በደን የተከበበ አካባቢ የማይጠገቡ ወንዞች፡፡ ከሰማው የረገጠው የሚወደው ስፍራ፤ ገዳም ጊዮርጊስ