Bete Amhara

Bete Amhara

Thursday, July 9, 2015

የዴቪድ ካን ኢየሩሳሌም እና የአማራ ጎንደር

የዴቪድ ካን ኢየሩሳሌም እና የአማራ ጎንደር
ለአማራ ልጆች ምን መጽሀፍ እንዲያነቡ ትመክራለህ ብባል (ምናልባት የመምከር አቅም ካገኘሁ) በመጀመሪያ ደረጃ አንብቡ የምለው ምጽአተ እስራኤልን ነው፡፡ በደራሲ ማሞ ውድነህ የተተረጎመውን ከአመታት በፊት አንብቤዋለሁ፡፡ እስራኤሎች እንዴት ባለ መራራ ትግል እና በተባበረ ወኔ ያችን አገር እንደፈጠሯት ሳስብ እስካሁን ድረስ ድንቅ ይለኛል፡፡ ከዚህ ቀደም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቢያነበው እና አገሪቱን ለመገንባት እንደመርህ እንዲጠቀምበት ብየ ነበር የምመኘው፡፡ አሁን ግን የመንገድ ለውጥ በማድረጌ አዲሱን ቤታችንን ቤተ አማራን እንዴት እንደምንገነባ ለአማራ ልጆች እንዲያነቡት እመክራለሁ፡፡ አንዳንዱ ታሪክ ያስለቅሳል፡፡ እስካሁን ድረስ እስራኤልን እንደ አገር ሲፈጥሩ የሄዱበት መንገድ እና ያደረጉት ውጣ ውረድ ስእሉ አይነህሊናየ ውስጥ አለ፡፡ ማድረግ ያለብንን ጥረት ከእነሱ ጋር ሳወዳድረው የእኛ በጣም ቀላል ነው፡፡ ዙሪያው በእንግሊዝ ጦርና ሽቦ የታጠረ ባህርን በመርከብ እና በጀልባ ሰርገው እየገቡ ሞትን አንገት ለአንገት ተናንቀው ነው ለእግራቸው ማረፊያ እንኩዋን ያገኙት፡፡ የእነሱ ስራ አየር ላይ ያለ ባላ ቆጥ እንደመስራት ነው፡፡
ከመጽሀፉ ባለታሪኮች አንዱ ታዲያ ዴቪድ ካን የሚባለው ጀግና ነው (ካሳሳትኩት አርሙኝ)፡፡ እንግሊዞች የጣሉትን ሰባራ መድፍ ጠግኖ በመተኮስ አረቦችን ትልቅ መሳሪያ እንዳለው አስመስሎ ያስፈራራ የነበር እና ብዙ ተጋድሎ ያደረገ ሰው ነው፡፡ ጥንት ሮማዊያን ኢየሩሳሌምን ሲገዙ የሰሩትን የመሬት ውስጥ ቦይ ቆፍሮ በማግኘት ውስጥ ለውስጥ እየተሸሎከለከ ብዙ ስራ የሰራ ነው፡፡ አንድ ቀን ታዲያ ኢየሩሳሌም ላይ ከባድ ውጊያ ገጠማቸው እና መሸሽ አስፈለገ፡፡ ጓደኞቹ ሸሹ፡፡ እርሱ ግን ኢየሩሳሌምን ስትወረር በአይኑ አያት፡፡ የኢየሩሳሌም ልጅ በመሆኑ የገዛ መንደሩ እየተወረረች ጥሎ መሄድን እንደክህደት ቆጠረው፡፡ ኢየሩሳሌምን መካድ አልሆንልህ አለው፡፡ ወደዋናው ጦርነት ገባ፡፡ ለኢየሩሳሌም ታማኝነቱን አተመላት---በደሙ፡፡ ምድሯም በታማኝ ልጇ ደስ ብሏት ይሆናል እንበል እና እንለፈው፡፡
በተመሳሳይ አማራን የሚያጠፋው ወያኔዎች በመጀመሪያ ሰይፉቸውን የሰነዘሩት ጎንደርና ወሎ ላይ ነው፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ጎንደር ላይ እየባሰባቸው ነው፡፡ እንደግራምጣ ሰነጠቋት፡፡ ከፊሉዋን ዋጧት፡፡ ልክ እንደአዞ አሁንም የቀረችውን እየሰለቀጧት ነው፡፡ የተወሰነውን ለሱዳን ሰጡት፡፡ ሰውን እስካሁኗ ሰአት ድረስ እያሳደዱ እየረሸኑት እና ማእከላዊ እያጋዙት ነው፡፡ ጎንደርን በቅርቡ ለመጨረስ ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ ያች “አያል በጎንደር ሽር እንበል ብሎኝ ነበር” ተብላ በክብር የምትንቆለጳጰስ ጎንደር የአዞ መንጋጋ ውስጥ ደም በደም ሆና እያጣጠረች ነው፡፡ ያች አማራነታችን ሁለት ሶስት ጊዜ ከጥፋት የዳነባት የመጨረሻ ምሽጋችን ራስዋ እየጠፋች ነው፡፡ ያች የታሪካችን ማማ፤ የአማራነታችን ትክክለኛ መገለጫ በአዞ እየተሰለቀጠች ነው፡፡ ጎንደርን ማን የሚያድን አለ? ለጎንደር በደሙ ማህተሙን የሚስቀምጥላት ማን አለ?
የኢየሩሳሌሙን ዴቪድ ካን ባሰብኩ ቁጥር በአእምሮየ እልፍ አእላፍ የአማራ ወጣቶች ይመጡብኛል፤ እልፍ አእላፍ የጎንደር ልጆች ይመጡብኛል፡፡ ጎንደርን ባሰብኩ ጊዜ የተባበረ አማራ ከፊቴ ድቅን ይላል፡፡ የተባበረ እና እንደ ዴቪድ ካን አንድ የሆነ መላው አማራ በግርማ ሞገስ ተምሞ ጎንደርን ከጅብ መንጋጋ ሲያስጥላት ይታየኛል…..
ጎንደር ወልቃይት ሆይ ብረሳሽ ቀኘ ትርሳኝ!
መለክ ሐራ ከቤተ አማራ