Bete Amhara

Bete Amhara

Thursday, July 9, 2015

ባህር ዳሬዋ

ባህር ዳሬዋ
ባህር ዳር ምን ትመስልሀለች ብትሉኝ ገነትን ትመስለኛለች ነው የምላችሁ፡፡ ከሶሰት አመት በፊት…”ባጃጅ ወደ ማንጎ ተውስደኛለህ” “ማንጎ መናፈሻ ነው ግባ” “ስንት ነው የምታስከፍለኝ” “…እእእ ሶሰት ብር ይበዛብህ ይሆን” “እሽ እንሂድ አምስት ብር አድርጌልሀለሁ” ፡፡ ማንጎ መናፈሻ ዳር ላይ የዘጌ ጀበና ቡና ጠጣሁ፡፡ ቡና እየጠጣሁ ሽሮ ፈሰስ አዘዝኩ፡፡ እውነት ለመናገር እንደዛን ቀን ሽሮ ጣፍጦኝ አያውቅም፡፡ ደግ ማዘዝ ነውር ሆኖብኝ ነው እንጅ…አስቤ ነበር፡፡ ከሁለት አመት በኋላ ስሄድ ያች የጀበና ቡና ቤት የለጭም፡፡ የዘጌ ቡና ልጠጣ እና ሽሮ ፈሰስ ልበላ ነበር ሃሳቤ፡፡ በጣም አዝንኩ፡፡ ባህርዳርን ራስዋን ያጣኋት መሰለኝ፡፡
ብዙ ጊዜ ባርዳር ስሄድ ማንጎ መናፈሻ ነው የምሄደው፡፡ ጣይቱ ላይ ቁጭ እልና ቢራየን እየኮመኮምኩ የጣናን ለም ነፋስ ሽውታ እየተቀበልኩ ቁጭ እላለሁ፡፡ ጣና የኔ መሆነን፤ ባህርዳር የኔ መሆኑን እዛ ላይ ቁጭ ብየ አስባለሁ፡፡ በቃ ምንም መናገር የማልችለው ስሜት ይውጠኛል፡፡ ያንን የመሰለ መዝናኛ ውስጥ የቢራና ለስላሳ ዋጋ ከሆቴሎች ብዙም የተለየ አይደለም፡፡ ጣይቱ ላይ ቁጭ ብየ የማየው ባህሩ ዳርቻ ላይ ወዳሉት የመቀመጫ ደረጃዎች ነው፡፡ መጽሀፍና ጋዜጣ የያዙ ሰዎች በአርምሞ ተቀምጠው አያለሁ፡፡ የሚነብ ያነባል፤ የሚጫወት ድምጹን ለስለስ አድርጎ ይጫወታል፡፡ ባህር ዳር ግን ማንበብ ስትወድ!
ከዛ አመሻሽ ላይ ወደባህል ቤቶች እሄዳለሁ፡፡ ባህርዳር በባህሏ የምትኮራ ከተማ ናት፡፡ ሁለት ሰአት ወይም ተኩል ላይ የባህል ምሽት ቤቶች ጢም ይላ፡፡ ከዛ ታሪካዊ ድራማዎች በጥኡም ሙዚቃና ውዝዋዜ እየተዋዙ ይቀርባሉ፡፡ ስለ ቴዎድሮስ፤ ስለ በላይ ሲተውኑ እና ሲሸልሉ እዛው ታሪኩ የሆነበት ቦታና ጊዜ የተገኘሁ ይመስለኛል፡፡ አበባ የሚመሳስሉ ልጃገረዶች ይመጡና ውዝዋዜውን ቅለልጥ ያደርጉታል፡፡ ና እንጅ ና በል ብለው እስክስታ እንዳወርድ ይጋብዙኛል፡፡ አንድ ቀን ሳልገልጽ የማላልፈው ነገር አየሁ፡፡ ሰው ሁሉ እየተነሳ ክብ ክብ እየሰራ እስክስተውን ያቀልጠዋል፡፡ በመሀል አዝማሪው ወደአገውኛ ቢት ይቀይረዋል፡፡ ያ አንዲት ወጣት ተነሳችና የአገውኛውን እስክስታ (ከወገብ በታች የሚጨምረውን) ታስነካው ጀመር፡፡ ሁሉም የራሱን እስክስታ ትቶ እሷን ዙሪያዋን ከብ ማጨብጨብ ጀመረ፡፡ የተቀመጥነው ሁሉ አልታየን ሲል ተነስተን እሷን እያየን እየተደነቅን ማጨብጨብ ጀመርን፡፡ ብቻ አልረሳውም፡፡
ሲነጋ ደግሞ ጭማቂ ቤቶች ጋር እሄዳለሁ፡፡ በረንዳ ላይ አንዱ ጭማቂ ቤት እቀመጥና አጠገቤ ካለው ሰው ጋር ወሬ እጀምራለሁ፡፡ እየጠጣሁ እያወራሁ፤ የሚልፈውን የሚያገድመውን እያየሁ፤ በዘምባባዎች እና ትናንሽ የጌጥ ዛፎች እየተማረክኩ እመሰጣለሁ…..ባህርዳሬዋ ገነት ትመስይኛለሽ እኮ…. ሌላ ጊዜ ደግሞ የባህል ምግብ ቤቶች እሄዳለሁ፡፡ ቋንጣ ፍርፍር እበላለሁ፡፡ የጀበና ቡና እጠጣለሁ፡፡ በተለይ አንድ ቤት አለ ሁሌ የምሄድበት፡፡ አሁን አሁን ግን ዋጋው እየተወደደብኝ ነው፡፡ ይሁን እንጅ በጣም ነው የምወደው፡፡ ግድጋዳው በሙሉ በባህላችን ጌጣጌጥ ያሸበረቀ ነው፡፡ እዛ ቤት ውስጥ ስሆን በጥንቱ በነገስታት እልፍይ ውስጥ
የተቀመጥኩ ነው የሚመስለኝ፡፡ ደግሞ ጸጥተኛ፤ የሰው ጆሮ ላይ የማይጮህ፤ የማይጋፋ…. ህዝብ፡፡
ባህርዳር ገነቴ… የአማራነት ፈርጥ፡፡ አራተኛዋ የአማራ ባህል ያበበባት ከተማችን፡፡ የአማራ የባህል ከተማ ባህር ዳር ነው፡፡ በባህችን እጅግ ጫፍ ላይ ደርሰን የነበረው ቤተ አማራ፤ አማራ ሳይንት፤ ላኮመልዛና አንጎት ላይ ነበር፡፡ ከዛ ወደሸዋ ሄደን እስከ አጼ ልብነ ድንግል ድረስ ስልጣኔያችን ያበበበት አማራነታችን ጫፍ ላይ የደረሰበት ነበር፡፡ በወራሪዎች ስልጣኔያችን ሲጠፋብን እና ህዝባችንም ሲጨፈጨፍብን ወደ ጎንደር ሄድን፡፡ ጎንደርም ላይ ለ350 አመታ ገደማ በስልጣኔ ርቀንና መጥቀን፤ በባህላችም አድግነ ኖርን፡፡ እንደገና በሰሜን ወራሪዎች ጠፍቶብን እና መንግስታችንም ወድቆብን ለ70 አመታት ዝብርቅርቃችን ወጥቶ ኖርን፡፡ በኋላም የወደቀው መንግስታችን በቴዎድሮስ ከትቢያ ተነሳ፡፡ ያም መንግስት ማእከሉ ተመልሶ ወደ ሸዋ ተዛወረ፡፡ ሸዋ አዲስ አበባ ላይም ወደ መጀመሪያው የአማራ ባህል ማበብ እንደገና መበልጸግ ጀምሮ ነበር፡፡ በኋላ ግን የውጭው ባህል እና ሌላውም እየጠጫጫነው ሙሉ በሙሉ የጥንቱን ለዛውን ማስመለስ ሳይችል ቀረ፡፡ ዶናልድ ሌቪን ሸዋን እና ጎንደርን ሲያወዳድር አማሮች ጎንደርን እንደጥንት ባህላቸው ተምሳሌትንተ ያይዋታል፤ የራሳቸው ብቻ ስለሆነች ይመኩባታል፤ አዲስ አበባ ግን የውጭውና ሌላው ባህል ጫና ስላለባት የጎንደርን ያህል አይኮሩባትም ብሉ ትዝብቱን አስፍሯል፡፡ አሁን ግን ባህርዳር የአማራ ባህል አብቦባታል፡፡ ለዚህም ምስጋና ይገባታል፡፡
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከዮርዳኖስ ወንዝ ያመጡትን ጸበል ጣና ላይ አፍስሰው ባህር ዳር የወደፊቱ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ትሆኛለሽ ብለዋል ይባላል፡፡ ከትልልቅ ሰዎች ነው የሰማሁት---ምን ያህል እውነት እንደሆነ አላውቅም፡፡ ትንቢቱ እውነት ከሆነ ግን ምናልባት የወደፊቱ የቤተ አማራ ዋና ከተማ ልትሆን ትችላለች ማለት ነው፡፡
ባህርዳሬ ብዙ ብጽፍልሽ ደስ ባለኝ፡፡ ግን እንደምፈልገው ልገልጽሽ አልቻልኩም፡፡ የተሻለ መጻፍ የሚችሉ የቤተ አማራ ልጆችን እንጠብቅ እስኪ፡፡