Bete Amhara

Bete Amhara

Saturday, July 18, 2015

ዐማራን ምን ነካው!

ዐማራን ምን ነካው

ዐማራን ምን ነካው ሲበዛ ጠላቱ ፣
ዘራፍ እምቢ ብሎ አለመነሳቱ ፤
ምን ነካህ ወገኔ እስኪ ተጠየቅ ፣
ፍራት ነው ትዕግስት ቁርጡን እንወቅ፤
አስተዋዩ ዐማራ የጀግኖቹ ዘር ፣
ለጠላት እጅ አይሰጥ የማይበገር ፤
ሲዋደቅ የኖረው ለዳር ለድንበሩ ፣
ቁርኝቱ ታላቅ ለኢትዮጵያ አገሩ ፣
ለጥቅም አይሸጥ ነፃነቱ ክብሩ ።
መሬቱን ሲቀሙት ከጎንደር ከወሎ ፣
ምንም እንዳልሆነ ፀጥ ረጭ ብሎ ፤
ደግሞ ይባስ ብሎ ዐማራ ተሣዶ ፣
ለዘር ፖለቲካው አረጉት ማገዶ ፤
ወልቃይትም ለቅሶ : ጠገዴም ዋያታ ፣
ከተማ ገጠሩ : በርከቶ ጫጫታ ፣
ሲረግፍ እንደቅጠል ዐማራ ሲመታ ።

ነፈሰጡሯ ታርዳ : ሽሉ ሲጋደም ፣
በደኖ : አርባጉጉ ፤ አሰቦት ገዳም ፤
ትልቅ ትንሽ አይል ለሕፃን አይራራ ፣
የዐማራውን ጨቅላ ሲመትሩት በካራ ፣
ገደል ሲጨምሩት ከነነፍሱ ዐማራ ፣
በአሶሳ : በወተር : ብዙ ግፍ ሲሰራ ።
ከእንስሳ ባነሰ ሲያርዱት ሲገሉት ፣
ከማሳው : ከቀየው ሲያፈናቅሉት ፣
ሀብት : ንብረት ዘርፈው ጥሪት ሲያሳጡት ፣
በአባይ አንደበት ስሙን ሲያጠፉት ፣
“ጨቋኝ ነው ጡት ቆራጭ” ብለው ሲያስጠሉት ።
እስከመቸ ይሆን ይሄ ወይኔ ወይኔ!
ዕቅዱን በተግባር ሲያሳካ ወያኔ ፣
ገዳማት ሲፈርሱ እንዳይሄድ ምናኔ ።
ዐማራን ምን ነካው ? ዐማራ ምን ሆነ ?
ለስንቱ እንደማይተርፍ በራሱ ጨከነ!
ፍራት ነው እንዳልል የሌለ ባባቱ ፣
ትዕግስት እንዳይባል ሲያስወጡት ከቤቱ ፣
ገደል ሲጨምሩት ሲያርዱት በሱነቱ ፣
ሁሌ እንዳለቀሰ በዚህ መሰንበቱ ፣
አልገባኝም ጭራሽ የዐማራ ስሌቱ?
የገጠመን ጠላት ይሉኝታ ቢስ ሆኖ ፣
ከምድር እንድንጠፋ አቅዶ ወስኖ ፤
ጠላት እያስነሣ በቆላ በደጋ ፣
ሁሌ ሲያሳድደን የዘረኛ መንጋ ፤
ጎጠኛ ወያኔ ባልተሞረደ አፉ ፣
“ዐማራ ጠላት ነው” እያሉ ሲፅፉ ፣
መቻል ደግ ነወይ ከልክ እያለፉ ?
ወያኔ ላይገደው የዐማራ ሥቃይ ፣
በትዕግስት ማለፉ መልስ ይሆናል ወይ?
ከእንግዲህ ይበቃል ተነሣ ወገኔ ፣
ራስህን አድን ከጨካኝ ወያኔ ።

by Mussa Muhabbet ZeWollo