Bete Amhara

Bete Amhara

Wednesday, July 8, 2015

ለአንዳንድ ወቅታዊ ጥያቄዎች የተሰጡ መልሶች

ለአንዳንድ ወቅታዊ ጥያቄዎች የተሰጡ መልሶች
=====================================
የቤተ አማራን የራሱን መንግስት የመመስረት ውጥን ሀሳብ ለህዝብ ካቀረብን ጀምሮ መደናገጥ፤ መደሰት፤ መደነጋገር እና መመራመር ተስተውሏል፡፡ ብዙ ወገኖችም የተለያዩ ጥያቄዎች እያቀረቡ ናቸው፡፡ እነሆ አንገብጋቢ ናቸው ያልናቸው የተወሰኑ ጉዳዮች ላይ አጠር ያለ ማብራሪያ ፅፈናል፡፡
1. የሰንደቅ አላማው ነገር
በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም የሙስሊሙን ማህበረሰብ ማነገጋገር የማይቻል ቢሆንም የቻልነውን ያህል የሙሰሊም አማሮችን አስተያየት ለመሰብሰብ ሞክረናል፡፡ በውጤቱም ንጹሁ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዴራ የቤተ አማራ ቢሆን ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸውልናል፡፡ በዚህም ላይ አያቶቻችን ሀይማኖት ሳይለያቸው እዚህ አርማ ስር ለሀገራቸው የተሰው በመሆኑ ቤተ አማራ የራሱ አድርጎ ቢጠቀምበት የአያቶቻችንን ታሪክ ለማስታወስና ለወደፊቱም የአንድነት ምልክታችን ሆኖ እንዲያገለግል ይሻል፡፡ የሚቋቋመውም የቤተ አማራ መንግስት ሴኩላር በመሆኑ የማናቸውም ቤተ እምነት ምልክት ሊያርፍበት እንደማይገባ በፅኑ እናምናለን፡፡
2. አማራ በሀይማኖት የተነሳ የግጭት ታሪክ የሌለው ስለመሆኑ
አንዳንድ ሰዎች በስህተት የአጼ ቴዎድሮስን የወሎ ዘመቻና የጭካኔ ቅጣት የሀይማኖት ሽፋን ሊሰጡት ሲዳዳቸው እናስተውላለን፡፡ ነገር ግን ንጉሱ ወደወሎ ባደረጓቸው ዘመቻዎች የፖለቲካ እርምጃ እንጅ ምንም አይነት ሀይማኖታዊ እርምጃ አልወሰዱም፡፡ ወሎ ላይ ያደረጉት የትም ካደረጉት ቢተካከል እንጅ አይበልጥም፡፡ ንጉሱ የጎንደርን አብያተ ክርስቲያትና ንዋየ ቅዱሳት ሁሉ አቃጥለዋል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ሀይማኖቷ ፖለቲካዊ ጠርዝ በመያዝዋ የተፈጠረ ግጭት እንጅ ሀይማኖቱን የማጥፋት አጀንዳ አልነበረም፡፡ ንጉሱ ጎጃምም፤ ጎንደርም ሸዋም ላይ ተመሳሳይ ነገር ነው ያደረጉት፡፡ የወሎው ለየት ያለ ማብራሪያ ካስፈለገው እንኳ ስርዎ መንግስታዊ እንጅ ሀይማኖታዊ አይሆንም፡፡ እንደሚታወቀው የየጁ (ወሎ) መሳፍንት በጎንደር አድራጊ ፈጣሪ ሆነው ለ71 አመታት ስልጣን ላይ ቆይተዋል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ደግሞ የቋረኞችን ቡድን ይዘው ነው የመንግስትን ስልጣን ከየጁ መሳፍንት የተረከቡት፡፡ በዚህም የተነሳ ፖለቲካዊ ቁርሾው እስከ ንጉሱ እለተ ሞት ድረስ ሲያገረሽ ቆየ፡፡ ይህ ያለና የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ በምንም መንገድ ግን ከእስልምና ጋር አይገናኝም፡፡ ይልቅ ንጉሱ ቀልባቸውን መሳት የጀመሩት ወሎን ገትሮ ይዞላቸው የነበረው ቃድሶ የተባለው ወሎየ ሙስሊም በተቃዋሚዎች ከተገደለባቸው በኋላ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ቃድሶን እጅግ ይወዱት ነበር ይባላል፡፡
3. ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ አማሮች ምን ይበጃቸው?
በእርግጥ ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ አማሮች እየኖሩ አይደለም ያሉት፡፡ መኖር ያለስጋትና ፍርሀት መኖርን ስለሚያካትት እነዚህ አብራኮቻችን እየኖሩ ነው ማለት ይከብዳል፡፡ ምናልባት እስከ ህይወታቸው ለመቆየት ይጣጣራሉ ብለን ብንረዳው ይሻላል፡፡ ወደፊት ነገሩ እየጠነከረና የቤተ አማራ መንግስት እውን መሆኑ ሲቃረብ ሊከሰቱ የሚችሉ ነገሮችን አሁን ላይ ሆኖ ይህ ነው ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ ለዚህ ይበጃሉ ብለን የምናስባቸው ነገሮች ሀ) በወደፊቱ የቤተ አማራ መንግስት ውስጥ የተለያዩ ማህበረሰቦችና ግለሰቦች እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ የእነዚህን ደህንነትና ዋስትና በማናቸውም ረገድ በመጠበቅ ሌላ ክልል የሚኖሩትን ተመሳሳይ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው መጣር ለ) በሌላ ክልል የሚኖሩት ወደ ቤተ አማራ መምጣት የግድ በሚሆንበት ጊዜ የዛኛው ክልል ቤተ አማራ ውስጥ የሚኖሩትን በሰላም እንዲያገኝ እኩል በእኩል መጣር፡፡ ሐ) በሌላ ክልል የሚኖሩ አማሮች ለማንኛውም ነቅተውና ተደራጅተው ሁኔታውን በንቃት መከታተልና ከዋናው እናት ምድራቸው ህዝብ ጋር በሚቻለው መንገድ ሁሉ ተጣምሮ ራስን መጠበቅ፡፡ መ) ከዚህ የከፋ ነገር ከተከሰተ በደል ፈጻሚው ወገን ከቤተ አማራ ጋር ሊኖረው የሚችለውን መልካም ጉርብትናም ሆነ ግንኙነት አደጋ ውስጥ መጣሉን ይገነዘባል ብን እናምናለን፡፡ ሠ) ቤተ አማራ ከመመስረቱ በፊት አንዳች ጉዳት ቢደርስባቸው ከወትሮው በተለየ ነቅቶ ጉዳዩን የሚከታተል ቤተአማራ ስላለ ለአለማቀፍ ህዝብ ማሳወቅ እንችላለን፡፡
4. ቤተአማራና የአንድነት ሀይሉ እንዴት ይስሩ?
በቤተ አማራ እምነት የአንድነት ሀይሉ የሚያደርገው የኢትዮጵያን አንድነት የማስጠበቅ እንቅስቃሴ የሚደገፍ ነው፡፡ ይህ ሀይል እድል ቀንቶት የአማራ ደህንነትና ህልውና ተጠብቆ ለ24 አመታት የተነጠቀ ዜግነቱ የሚመለስበትን ሁኔታ ማመቻት ከቻለ ቤተ አማራ የሚደግፈው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ሁለቱም እየተጋገዙ እንዲሰሩ እንመኛለን፡፡
5. በአማራ መገንጠልና እንደ አማራ መደራጀት መካከል ያለው ልዩነት
አማራ በአሁኑ ወቅት እንደአማራ የሚደራጅበት ምንም እድል የለም፡፡ ላለፉት 23 አመታት ተሞክሮ አልተሳካም፡፡ ስለዚህ የአማራ እንደኣማራ መደራጀት ውጤት እንጅ ሂደት ሊሆን አይችልም፡፡ ይህም ማለት አማራ ሊደራጅ የሚችልበት መቆሚያ የለም፡፡ ምናልባት ሰማይ ቤት ሄዶ ይደራጅ ብለው የሚያሾፉ ከሌሉ በስተቀር፡፡ አማራ እንደአማራ መደራጀት የሚችለው የራሱን ቤተ አማራ መንግስት ሲያቋቁም ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በየትኛውም መንገድ አማራ ከነጻ መንግስትነቱ በፊት የሚደራጅበት ምንም ዘዴ የለም፡፡ ስለሆነም ሊሆን በማይችል ነገር ላይ አማራን በአማራነቱ ማደራጀት አለብን እያልን ፈረሱን በጋሪው አንጎትትም፡፡
6. የኢትዮጵያ አንድነት ይመጣል እያልን እስከ ዳግም ምፅአት እንጠብቅን?
በቤተ አማራ እምነት የቤተ አማራ ነጻ መንግስትነት ታስረው ጨለማ ውስጥ ተቆልፎባው የሚማቅቁና ሳር እየበቀለባቸው ያሉ ወገኖቻችንን ነጻ ማውጣት ይችላል፡፡ እነዚህ ምርጥ የሆኑ ወገኖቻችን ከሚኖሩበት ሲኦል ነፃ መውጣት የሚችሉት በቤተ አማራው የነጻ መንግስትነት እውጃ እግረ መንገድ ላይ ነው፡፡
7. የድንበርና የግዛት ወሰን ጉዳይ
ከብዙ ወገኖች ጋር በተደረገ የሃሳብ ፍጭት ቤተአማራ ጥንታዊ በታሪክ የሚደገፈውን የግዛት ወሰኑን አስከብሮ መንግስትነቱን እንደሚያውጅ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ጉዳዩ ውስብስብ ከመሆኑ አንጻር በሂደት የሚቋጩ ነገሮች አሉት፡፡ በድርድርና ሰጥቶ መቀበል መርሆች የሚፈቱ የድንበር ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡
8. በእናት ወይም በአባታቸው ብቻ አማራ የሆኑ ምን ይሆናሉ?
እንኳን በትውልድ አማራ የሆነ ይቅርና ማንም ከቤተ አማራ ወገን የማይወለድ በቤተ አማራ መንግስት ውስጥ መኖር እስከፈለገና እስከፈቀደ ድረስ ሙሉ መብቱ ነው፡፡
9. ቋንቋ
የቤተ አማራ መንግስት ለተለያዩ ቋንቋዎች ሙሉና ልባዊ እውቅና ይሰጣል፡፡ ሁሉም ንኡሳን ነገዶች በራሳቸው ቋንቋ የመማር ሙሉ መብትና ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ ቤተ አማራ እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚበለጽጉበት እንጅ የሚዋጡበት አይደለም፤ አይሆንምም፡፡ ለዚህም በቤተ አማራ የሚኖሩ እንደ ወይጦና ቅማንት እንዲሁም አገው ያሉ ነገዶች እስካሁንም ድረስ ከእነ ህልውናቸው ይገኛሉ፡፡ ወደፊትም እነዚህንና ወደ ቤተ አማራ ይጣቃለላሉ ተብለው የሚታሰቡትን እንደ ጉራጌ፤ ሀድያ፤ ኦሮሞ፤ ከንባታ፤ ከፋ፤ አፋርና ሌሎችንም ሙሉ በሙሉ የሚንከባከብና የሚያበለጽግ መንግስት ይቋቋማል፡፡
10. አማራ ለምንድን ነው የሚገነጠለው?
አማራ የሚገነጠለው መጀመሪያም ስለተገነጠለ ነው፡፡ መጀመሪያውኑም አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ውስጥ ዜግነት ስለሌለው ነው፡፡ የአሁኑ ጉዳይ በሀሉም ነገር በአገዛዙ ከኢትዮጵያ የተገነጠለውን ህዝብ አሰባስቦ መንግስት ወዳለው የራሱ አካልነት የማሸጋገር ሂደት ነው፡፡ አሁን እየተወራ ያለው የመሬት መለየት ነው፡፡ ባለፉት 24 አመታት ከኢትዮጵያ በብዙ ዘርፎች ተገንጥሏል፡፡ በባህሉ፤ በቋንቋው፤ በህልውናው፤ በማንነቱ፤ በስራውና ኑሮው፤ በህይወቱ፤ በስነጥበብ ሀብቱ፤ በፖለቲካዊ ተሳትፎው፤ በሀይማኖቱ፤ በታሪኩና በሌሎችም ነገሮች ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ሆነ ተብሎ ተገንጥሏል፡፡ ስለሆነም ቤተ አማራ ያነሳው ጥያቄ ይህንን በሁሉም ነገር ተገንጥሎ አገርና መንግስት አልባ የሆነ ህዝብ ባለ መንግስት ማድረግ ነው፡፡ የአማራ መገንጠል መንግስት አልባ የተደረገውን መጻተኛ ህዝብ መንግስት እንዲኖረው የማድረግ እርምጀ ተደረጎ ይወሰድ ዘንድ እናሳስባለን፡፡
11. አሁንም በኢትዮጵያ አንድነት ስም አማራው ፍዳውን ይብላን?
ፈፅሞ፡፡ አማራ ለዚህች አገር ያለውን ሁሉ ከፍሎ ጨርሷል፡፡ ሁሉንም ያለውን ነገር ከፍሎ በመጨረሱም ራሱ መጥፋት ጀምሯል፡፡ ከአሁን በኋላ አማራ መድማትና መሞት ካለበት ለራሱ ህልውና ብቻ ይሆናል፡፡ የራሱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ፡፡ ኢትዮጵያ የአማራ ሸክምነቷ አብቅቷል፡፡ ይህችን አገር አንድ ማድረግ የፈለገ ወላ ሱማሌን አልያ ኦሮሞን አስተባብሮ አንድ ማድረግ ይችላል፡፡
12. ተገንጥየ ምን ልበላ ነው?
አማራ የሚያመርተው ምርት ቤተ አማራን መግቦ ለሌላም እንደሚተርፍ የታወቀ ነው፡፡ በሳይንስ ሲደገፍ ደግሞ የበለጠ ይለማል፡፡ አምላክ ይመስገን ምድራችን የማያበቅልልን ነገር የለም፡፡ እርሱን በፍቅርና በትጋት እያለሙ መኖር ብቻ ነው፡፡ ማንም ሰው መርምሮ ቢረዳው ወደ ቤተ አማራ ጤፍ አይጫን፤ በቆሎ አይጫን፤ ባቄላ አይጫን፤ የቅባት እህል አይጫን፤ እንስሳ አይጫን ምን አይጫን፡፡ በተቃራኒው ህዝባችን በጠኔ ፍዳውን እየበላ እነዚህና ሌሎች ምርቶች ወደተቀረው ኢትዮጵያ ክፍሎች፤ ወደ ሱዳንና ሌሎች አገሮች ይጫናሉ፡፡ ይልቅም ሀብታችን የወያኔ መድለቢያና ዘራችንን የማጥፊያ መሳሪያ መግዣ ነው የሆነው፡፡
መለክ ሐራ ከቤተ አማራ