ጎጃም፡ አማርኛ፡ ቅኔ፡ ሙዚቃ፡ ፍቅር እስከ መቃብር
አማርኛ ከ51 የአለም ዋና ዋና ቋንቋዎች አንዱ ሲሆን በ45ኛ ደረጃ ተቀምጦ ይገኛል (http://www.assam.org/)፡፡ አማርኛ የራሱን (የወላጅ እናቱን ግእዝን) ፊደል በመጠቀም ዘመናዊነትን የተቀላቀለ ሰፊ ቋንቋ ነው፡፡ ከአረብኛ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኝ ትልቁ የሴሜቲክ ቋንቋ ነው፡፡ ማለትም አማርኛ ከአረብኛ ቀጥሎ ትልቁ የሴማዊያን ቋንቋ ነው ማለት ነው፡፡ የአማርኛ ቋንቋ በስነ ጽሁፍ ረገድ በጣም ያደገ ነው፡፡ ይህም የአማራ አስተዋጽኦ ነው፡፡ በራሳቸው ፊደልና ቋንቋ ከሚጠቀሙ ጥቂት አገራት አንዷ ኢትዮጵያ እንድትሆን ያስቻለ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ዘመን የአማርኛ ስነጽሁፍ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ጎጃም ነው፡፡ በጠቅላላው አማራ በተለይ ደግሞ በጎጃም ሀሳብን በጽሁፍ መግለጽ ትልቅ ልማድ ነው፡፡ የዚህም ማህበራዊ ልማድ አማርኛችን የጽሁፍ ቋንቋነቱ እንዲዳብር አድርጓል፡፡ ይህንንም ስንል በቁጥር ከፍተኛ ዘመናዊ ጸሀፍት የወጡት ከጎጃም ነው፡፡ እናመሰግናለን፡፡
ቅኔ ትልቁና ጎጀም በተለይ ጠብቃ ያቆየችልን እና ያበረከተችልን የአማራነታችን ጸጋ ነው፡፡ ሰምና ወርቅ የሆነው አማራ ትክክለኛ መገለጫው ቅኔ ነው፡፡ ቅኔ ለረጅም አመታት መማርን እና ልዩ የመረዳት ጸጋን የሚጠይቅ ነው፡፡ በቅኔ ረቂቅ የሆነ እሳቤን የምንኖርበት ነው፡፡ በአለም ላይ የኛን ያህል የዳበረ ሰምና ወርቅ ግጥምና ንግግር ያለ አይመስለኝም፡፡ የማገኛቸው የውጭ አገር ሰዎች ስለ ቅኔ ስነግራቸው መጀመሪያ ግር ይላቸዋል፡፡ ቆይተው ግን በጣም ይደነቃሉ፡፡ ይህ እንግዲህ የምናብ እድገትን የሚያመለክት ነው፡፡ በቅኔ ነገራትን እያመሰጠሩና እየተራቀቁ ለጥበብ መኖርና በጥበብ መኖር የአማራ ባህል ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ አማርኛ በጣም ጥልቅ ቋንቋ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ አሁን አሁን እየተረሳ በተራ ንግግር እየተተካ መጣ እንጅ በድሮ ጊዜ ንግግርን በቀጥታ መናገር ብዙም ጥሩ አልነበረም ይባላል፡፡ የንግግር ብስለት የሚለካው ነገርን በምስጢር በመነጋገር ነበር፡፡ ካልተሳሳትኩ ትልልቆች እንደ ነገሩኝ ይህንን የድሮ ንግግር ዘዴ ሰለመን ብለው ይጠሩታል፡፡
በሙዚቃም ጎጃም ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በእርግጥ ጎንደር በዚህ በጣም የታወቀ ይመስላል፡፡ አንዲት አሜሪካዊት ፕሮፌሰር ያጠናችውን ጥናት (“The Musician and Transmission of Religions Tradition: The Multiple Roles of the Ethiopian Dabtara”, 1992) እዚህ ላይ እጠቀማለሁ፡፡ ወጣቶች የሚማሩት አንዱና ትልቁ እውቀት የዜማ እውቀት ነው፡፡ ከሶስቱ በአንዱ ዜማ ቤቶች ይማራሉ፡፡ ዋናውና በጣም የታወቀው ዜማ ቤት በደቡባዊ ጎንደር፤ ከደብረታቦር 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ቤተልሄም የዜማ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ ታዋቂነት የነበረውና በግራኝ ጦርነት ጊዜ የያሬዳዊ ዜማን ከመጥፋት ያዳነልን ዜማ ቤት ነው፡፡ ሁለተኛውም ዜማ ቤት እዚሁ ደቡባዊ ጎንደር የሚገኘው ቆማ ፋሲለደስ ገዳም ነው፡፡ ይህም በ17ኛው መቶክፍለ ዘመን መጀመሪያ ማለትም በአጼ ፋሲለደስ እርዳታ መሆኑ ነው እንደተመሰረተ ይነገራል፡፡ ሶስተኛው ደግሞ አቻበር የሚባለው ሲሆን ከብሩር ማርያም ገዳም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ መገኛውም በሰሜናዊ ጎጃም ነው፡፡ የዜማ ስልቱም ከቆማ ፋሲለደስ ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡
ከቅኔ ወደ አማርኛ ስንመጣ ይህን እናገኛለን፡፡ Job Ludophus (1682) በጻፈው የኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ የምእራባዊያንን አካደሚያዊ ስልት የተከተለ ታሪክ ስለ አማርኛ እና የአማራ ግዛቶች የቋንቋ አንድነት የሚከተለውን ብሏል፡፡ “To the Amharic Language, those of the Neignbouring Kingdoms come the nearest; though their Dialects are different one from another; for that of Bagemeder is peculiar: Angota, Hata, Gojam, and Shewa, use a Dialect common to one another” (ገጽ 80):: Hata ያለው የትኛውን አካባቢ እንደሆነ ማወቅ አልቻልኩም፡፡ ይህ ጸሀፊ የኢትዮጵያ ታሪክ ብሎ ሲጀምር በአማራ ግዛት ትልቅነት እና ስልጡንነት ነው የሚጀምረው፡፡ “Amhara is now the most noble kingdom of Ethiopia” (ገጽ 13) በማለት:: ይህም ከዚህ ጸሀፊ ቀድሞ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው አባ ጀሮሜ “The inhabitants of the Kingdom of Amhara are the most civilized and polite” ካለው ጋር የሚጋጠም ምስክርነት ነው፡፡
ስለጎጃም ስንጽፍ እንግዲህ የቅኔ ቤቶችን እንጠቅሳለን፡፡ ከዚህም ዲማ ጊዮርጊስ ዋናው አድባራችን ነው፡፡ አለም ያወቀው ስለሆነ ዛሬ ስለዲማ ብዙ አልልም፡፡ ከዚህ ይልቅ ከዲማ ስለመነጨው ፍቅር እስከ መቃብር ነው ትንሽ ማለት የወደድኩት፡፡ ፍቅር እስከመቃብር ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ በአማራ ላይ ስለደረሰው አስተዳደራዊ በደል እንዲሁም ፍቅርና እሴት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ መጽሀፍ ነው፡፡ ፍቅር እስከመቃብር በወጣበት ዘመን የነበሩ የአማራ ጥላቻ አቀንቃኞች አማራ ጨቆነን ሲሉ ያንን መጽሀፍ አለማንበባቸውን ቢያነቡትም አለመረደታቸውን ያመለክታል፡፡ ሀዲስ አለማየሁ ትንቢት በሚመስል መልኩ አማራ ያለፈበትን ሰቆቃ በደንብ አስቀመጥውላቸው ነበር፡፡ ያንንን መከራ ያሳለፈ ህዝብ በምንም መንገድ ጨቁዋኝ እና ጠላት ተደርጎ ባልተዘመተበትም ነበር፡፡ ሳይረዱት ቀርተዋል ወይም ሆነ ብለው በተንኮል ጆሮ ዳባ ልበስ ብለውታል፡፡ በምንም ተአምር ፍቅር እስከመቃብርን ያነበበና በውስጡ የተገለጹትን የእውነታ ነጻብራቅ የሆኑ ታሪኮችን የተረዳ ለአማራ ሊያዝንለት እንጅ ጠላቴ ብሎ ሊነሳሳበት ባልተገባም ነበር፡፡ ግን እስካሁን ድረስ እኛ አማሮች የሚረዳን በማጣት በጠላትነት ተፈርጀን ቀረን፡፡ የእኛን ችግር የሚረዳ በመጥፋቱም ህዝባችን ለታላቅ ጥፋት ተዳረገ፡፡ ከውስጡ የወጡትም እንኳ ለመረዳት ይሸፈንባቸዋል፡፡ ያ የታሪክ ማማ የደረሰ እና ለአገር ጠላቶች አገር ሰርቶ በደሙ አጥሮ የሰጠ ህዝብ ዛሬ በወያኔ ሴራ በአለም ላይ ቁጥር አንድ ደሀ ህዝብ እንዲሆን ተደረገ፡፡
አሁን ግን የህዝባችን እጣ ፈንታ በቤተ አማራ ትውልድ ላይ ወድቋል፡፡ ሁሉንም አቅማችንን ተጠቅመን እንሰራለን፡፡ ህዝባችንን ከወደቀበት የታሪክ አዘቅት እናወጣለን፡፡ ከዘመነ መሳፍንት በፊት ወደ ነበረበት ማማው እንመልሰዋለን! ይህንን ባናደርግ ግን እኛ ራሳችን በታሪክ ፊት አሳፋሪ ቡትቶ ለባሽ ሆነን እንቀራለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ ከጎጃም ለበቀሉ ጸሀፍት የክቡር ሀዲስ አለማየሁን ፈለግ በመከተል በህዝባችን ላይ የሚደርሰውን ግፍ እንድትጽፉ እመኛለሁ፡፡ የትግል ግማሹ ስነ ጽሁፍ ነው፡፡ በደህና ቀን በአባቶቻችን ዳብሮ እና አድጎ የተሰጠንን አኩሪ ስነጽሁፋችንን በመጠቀም ወገናችንን እናንቃበት እናም ከፈጽሞ ጥፋት እንታደግበት፡፡ አማርኛን ለአማራ መድህንነነት እንጠቀምበት!
ጎጃም ቤተ አማራ