Bete Amhara

Bete Amhara

Wednesday, July 22, 2015

“አንች እየኮሰተርሽ እኔን ታሸክሚያለሽ”

“አንች እየኮሰተርሽ እኔን ታሸክሚያለሽ” ------የበላይ አማት
ከረጅም ጊዜ በፊት ካነበብኩት እንድ ምንነቱን የረሳሁት ጋዜጣ ላይ ይህንን አስታውሳለሁ፡፡ ጋዜጣው ላይ የቀረበው ጽሁፍ የበላይ ዘለቀ ጓደኛ እና አርበኛ የነበሩ ሰው የተናገሩት ነው፡፡ በላይ ዘለቀ ለምን አባ ኮስትር እንደተባለ ከዛ ጊዜ ጀምሮ ነው የማውቀው፡፡ ሙሉ በሙሉ ባላስታውሰውም ልቤ ውስጥ የቀሩት ታሪኮች እኒህ ናቸው፡፡ በላይ የጎጃምን ጦረኞች እየመራ ጸረ ጣልያን ፍልሚያ ሲያደርግ ከጓደኞቹ ጋር ብቻ አልነበረም፡፡ በባህላችን አንቱታ የሚቸራቸው እና የልጅ ባል የሚንቀጠቀጥላቸው ሰው አብረውት አርበኝነት ላይ ነበሩ፡፡ አማት ከልጃቸው ባል ጋር፡፡ እና በሶማ በረሀ ይመስለኛል ሰሳ (ድኩላ) እያደኑ ይመገባሉ፡፡ አማትና አማች፡፡ በመጀመሪያ አማት ይተኩሳሉ፡፡ ይስታሉ፡፡ ከዛ በላይ ይተኩሳል፡፡ ይገድላል፡፡ አሁንም እንደገና አማች ይተኩሳ፡፡ ይስታሉ፡፡ ከዛ በላይ ይተኩሳል፡፡ ይገድላል፡፡ በኋላ የሚገደሉት ሰሳዎች ሲበዙ አማት መሸከም ይጀምራሉ፡፡ በላይ ግን አሁንም ተኩሶ ይጥላል፡፡ አማት ይሸከማሉ፡፡ ከዛም እንዲህ አሉት “አንች እየኮሰተርሽ እኔን ታሸክሚያለሽ፤ ከዛሬ በኋላ ኮስትር በላይ ብየሻለሁ” አሉት፡፡ ከዛ ወዲህ አባ ኮስትር በላይ ዘለቀ ተብሎ ቀረ፡፡

እኒህ አርበኛ ይቀጥላሉ፡፡ ከአራቱ የእንግሊዝ ጀኔራሎች የቱ እንደሆነ አላስታውስም (ምናልባት ጀኔራል ዊንጌት ሳይሆን አይቀርም)---በበላይ የሚመሩት አርበኞች እና በዚህ እንግሊዛዊ ጀኔራል የሚመሩት የእንግሊዝ ወታደሮች ጣምራ ዘመቻ ያካሂዳሉ፡፡ በላይና ጀኔራሉ ኢላማ ተኩስ ይሞካከራሉ፡፡ በላይም ጀኔራሉን ያስከነዳዋል፡፡ በዚህ መሀል የበላይ አርበኞች የጣልያን ወታደሮችን እየገደሉ ሲጨፍሩ ያያል፡፡ በጣም ደነገጠ፡፡ እኒህ አባት አርበኛ ታዲያ የእንግሊዙን ጀነራል ሁኔታ ሲገልጹት “ነጭ ሲደነግጥ የበለጠ እንደሚነጣ የዛን ጊዜ ነው ያየሁት” ይላሉ፡፡

አምሐራ ማለት ነጻ ህዝብ ነው የሚለው መጠሪያችን የተፈተነበት እና ተፈትኖ ያለፈበት ጊዜ ቢኖር የአምስት አመቱ የጣልያን ወረራ ነው፡፡ ብዙ የአፍሪካ፤ የእስያ፤ እና የአሜሪካ ጎሳዎች (ህንድን እና ቻይናን ይጨምራል) በአውሮፓዊያዊያን ግዛት ስር ሲወድቁ በጠበመንጃ፤ በብርድ ልብስ፤ በሳህን፤ በስኒና ብርጭቆ፤ በመጋረጃና ምንጣፍ እንዲሁም በሰአት እየተታለሉ ነበር አገርና ህዝባቸውን የሸጡት፡፡ ወደ እኛ አገር ሲመጡ ግን ነገሩ የተለየ ሆኖ ነበር የጠበቃቸው፡፡ ስለሀገሩና ወገኑ ሞትን የማይፈራ፤ ጥቅም የማይደልለው ህዝብ አጋጠማቸው፡፡ መላው አማራ በነቂስ ለክብርና ለነጻነቱ ተዋደቀ፡፡ ከእነዚህ እልፍ ጀግኖች መካከል አንዱ የዛሬው ታሪካችን ዝክር በላይ ዘለቀና እና የጎጃም አርበኛ ሰራዊቱ ነው፡፡ ቤተ አማራ በጎጃም ሳምንት የነጻነታችን ፈርጥ አድረጎ ከሚያስቀምጣቸው አንዱ አባ ኮስትር በላይ ዘለቀ ነው፡፡

ይህ በላይ ዘቀ እና ጓደኞቹ የአምሐራ ልጆች ናቸው፡፡ የታሪክና ህዝብነታቸው ማንነት እርሱም በማንም የማይወረር (The Unconqourable) ነጻ ህዝብነት ፈተና ላይ በወደቀበት ክፉ ጊዜ የተገኙ፡፡ አምሐራ ነጻ ህዝብነቱ ይረጋገጥና ከነሙሉ ትርጉምና ክብሩ ይቀጥል ወይስ ይወረርና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነጻ ህዝብነቱ ይቋረጥ የሚል ሞትን የሚጠይቅ ውሳኔ መጣባቸው---በዘመኑ ለነበሩ መላው አማራ እናት እና አባቶቻችን፡፡ ከእነዚሁ አንዱ በላይ ነውና በዚህ አጣቂኝ ፈተና ውስጥ የወደቀው ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ነበረበት፡፡ በበኩሉ የአምሐራ ነጻ ህዝብነት በእርሱ ዘመን ሊገረሰስ እንደማይገባ ከጓደኞቹ ጋር መክሮ ዘክሮ ወሰነ፡፡ የአማራ ነጻ ህዝብነት መቃብራችን ላይ ብቻ ይገረሰሳል፤ ክንዳችንን ሳንንተራስ ምድራችንን ነጭ አይፈነጭባትም፤ ህዝባችንም ወደ ባርነት አይወርድም ብለው ተማምለው በረሀ ወረዱ፡፡ ይህም በላይ እልፍ የጎጃም ፋኖዎችን አስከትሎ ለአምሐራ ነጻ ህዝብነት ተዋደቀ፡፡ አባቶቻችንም በደማቸው የአማራን አይበገሬነት እና አይነኬነት አረጋገጡ፡፡ በማንም የማይወረር መሆኑን አረጋገጡ፡፡ ያች ከጥንት የነበረች የነጻ ህዝብ ደም ከትውልድ ወደ ተውልድ ስትሸጋገር የበላይ የደም ስር ውስጥ ተገኘች፡፡ እርሱም አላሳፈራትም፡፡ ልክ ሌሎች አቻዎቹ እና ጓደኞቹ እንዳደረጉት ሁሉ እርሱም ነጻ ህዝብነታችን ሳይቋረጥ ለእኛ እንዲደርስ አደረገ፡፡

በላይ ዘለቀ በአለም ታሪክ ያልተንበረከከው የአማራ ህዝብ ልጅ ነው፡፡ እኔም የማይንበረከክ ህዝብ ልጅ ነኝ እና በደሜ ውስጥ የበላይ የአምሐራ ነጻ ህዝብነት ደም አለች፡፡ ለእርስዋ መቀጠልም ዛሬ ወገኔን በማንቃት እየተጋሁ ነው፡፡ ነገ ደግሞ ለአማራ ነጻ ህዝብነት ስል እገብራታለሁ፡፡ እኔ መለክ ሐራ የነጻ ህዝብ ልጅ ነኝ ስል የጎጃም፡ የሸዋ፡ የወሎ፡ እና የጎንደር አባት እና እናቶቸ ደም ሰጥተውኛል ማለት ነው፡፡ ደም የተከፈለብኝ የመስዋእትነት ልጅ ነኝ ማለት ነው፡፡ ወይም በደም ውል የተፈረመ ነጻነት የተቀበልሁ ሰው ነኝ ማለት ነው፡፡ ከእነዚሁም በላይ ዘለና እና ጓደኞቹ የከፈሉልኝን ደም ዛሬ የምዘክረው ነው፡፡ እኔ እንድኖር ሌላ ሰው ሞቶልኛል፡፡ እኔም ነገ ልጀ እንዲኖር አድክምለታለሁ፤እሞትለታለሁ፡፡ እኔም ነገ ልጀ እንድትኖር እድክምላታለሁ፤ እሞትላታለሁ፡፡ ክብርና ነጻነቱን በሞቱ የሚገዛ ህዝብ ልጅ ነኝ፡፡ ከዚህም ተነስቸ ትምክህተኛና ኩሩ መሆኔን በአደባባይ አውጃለሁ!

ሰማይና መሬት ሙሉ ምስጋና ለበላይ ዘለቀ! ሰማይና ምድር ሙሉ ክብርና ምስጋና ለጎጃ አርበኞች! ሰማይና ምድር ሙሉ ክብርና ምስጋና ለመላው አርበኛ አማራ ህዝብ ይሁንልኝ፡፡ እኔን ትምክህተኛ ያደረጋችሁኝ ለእኔ በከፈላችሁት ደም ነው፡፡ የደም ዋጋየ ትምክህትና ኩራት ናት፡፡ ማንም የትምክህትን ትርጉም ባለማወቁ ትምክህተኛ ብሎ ሊያሸማቅቀኝ ቢሞክርም እኔ ግን ለእኔ ትምክህተኛነት የሰውነት ምልክቴ ናት፡፡ ምን እንደተከፈለልኝ ጠንቅቄ የማውቅ ነኝ እና ደም የተከፈለባትን የዘለአለም ቃል ኪዳኔን ትምክህቴን በከንቱ አልጥላትም፡፡

ሁላችሁም የነጻ ህዝብ ልጆች የበላይ አደራ አለባችሁ…….
ጎጃም ቤተ አማራ