Bete Amhara

Bete Amhara

Sunday, July 12, 2015

ጎንደር፡ ቅማንትና “ጭቆና”

ጎንደር፡ ቅማንትና “ጭቆና”

ከአማራነታችን ፈርጦች አንዱ የሆነው አገር ጎንደር ገና ከማለዳው ጀምሮ መታመሱ የዘወትር ህመሜ ነው፡፡ በደርግ ተረሽነው ያለቁ ወጣቶችን ሁኔታ እስከአሟሟታቸው ታሪክ በጣም ስሰማ ነው ያደግኩት፡፡ እስከነፍሳቸው ገደል የተጣሉ፤ እና እስከነፍሳቸው በዶዘር አፈር የተደፋባቸው ቦታዎችን ሁሉ ሰምቻለሁ፤ ሄጀም አይቻለሁ፡፡ እናቶች “ኑ እንጨት እንልቀም” ብለው ወደጫካ ሄደው ያለቅሱ ነበር አሉ--ማልቀስ ስለማይፈቀድ፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆን አንድ ጊዜ ያጋጠመኝን ታሪክ ላውጋችሁ፡፡ በአንድ የባህር ማዶ ጥናታዊ ጉባኤ ላይ አንድ ፕሮፌሰር ተዋወቅኩ፡፡ ስንጫወት እያዘነ “በኢህአፓ ሰበብ ወጣቶች ሲያልቁ ያመለጥኩ ነኝ” አለኝ፡፡ ቀጠለ እያዘነ “አሁን ወደጎንደር አልሄድም፤ ቤተሰቦቸን ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ አድርጌ ነው የማገኛቸው፡፡ ጎንደር ስሄድ በለጋነታቸው የተቀጩት ጓደኞቸ እናቶች ሲያዩኝ “የእኛም ልጆች ቢኖሩ እንዳንተ ነበር የሚሆኑልን እያሉ እያለቀሱ እና እኔም እየተረበሽኩ ተቸገርኩ” አለኝ፡፡ እናም አለ “የጓደኞቸን እናቶች አላስለቅስም ብየ ጎንደር መሄድን እርም ብየ ተውኩ”፡፡

ጎንደር በወያኔ ወረራ ስር ከወደቀች በኋላ የሆነውን ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ በአደባባይ በጥይት ከመጨፍጨፍ፤ በገላጣ እስከመረሸን እንዲሁም ሰዎችን እስከመሰወር፤ መሬቱን በመዝረፍ፡ ወዘተርፈ…..
አሁንም የጎንደር ስቃይ አልበረደም፡፡ ጭራሽ እየባሰበት መጣ፡፡ አንዱን ህዝብ እንደግራምጣ በመሰንጠቅ የጠብና የውዝግብ ምድር አደረጉት፡፡ ይህም የቅማንት ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ ቅማንት አማራ ነው፡፡ ከአማራ ያነሰም ሆነ ከፍ ያለ ማንነት የለውም፡፡ ቅማንት ሁሉንም የአማራ ባህልና ባህርያት እንዲሁም ታሪክ የሚያሟላ የጎንደር አማራ ነው፡፡ ከመልኩ፤ ከእምነቱ፤ ከቋንቋው፤ ከጸባዩ፤ ከኩራቱ እና ከአኗኗሩ ሁሉ ቅማንት አማራ እንጅ ሌላ መጠሪያ ሊሰጠው አይችልም፡፡ ዛሬ አማራ ቅማንትን ጨቁኖታል የሚለው የወያኔ ከፋፋይ ሴራ ለእኔ የዘመኑ ጸረ ህዝብ ቀልድ ነው፡፡ በህዝብ የዛሬ ማንነት እና በወደፊት ህልውና የተቀለደ የጠላቶቻችን ቀልድ፡፡ አማራን ማዳከም በሚለው የወያኔ ስትራቴጅ ስሌት ውስጥ የተገኘው ቅማንት ነው፡፡ ቅማንትኛ የሚባል ቋንቋ አለ/ነበረ፤ የተለየ እምነት ነበር የሚሉ አፈታሪኮችን በመስማት አንዱን አማራ ነጣጠሉት፡፡ ያው ይህ እግዲህ አማራን አዳክሞ መሬቱን መውሰድ የሚለው የወያኔ አላማ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ወያኔ እንኳን ቅማንትን ሊያፈቅር በራስዋ በትግራይ ለሚኖሩ 600 000 (ስድስት መቶ ሽህ) የኤሮብ ጎሳ እና ለኩናማ ጎሳ አንዳች እድል ያልሰጠ ይልቅም ከምንም ነገር ውጭ ያደረገ ረጋጭ ነው፡፡ በራሱ ቤት ያሉትን ኤሮብና ኩናማን መብት የነሳው ወያኔ ተከዜን ተሻግሮ የቅማንትን ወዳጅነት ፈለገ ማለት ዘበት..…የዘበት ዘበት….ደባሪ ቀልድ ነው፡፡

አማራ ቅማንትን ጨቁኗል የሚለው ቀልድ አንድ ነገድ ራሱን ጨቆነ የሚል የመጀመሪያው ቀልድ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እኔ የምፈራው ኩሩው የቅማንት አማራ ልጆች አሁን እየተፈጠረላቸው ባለው የጭቆና ተረት ለወደፊቱ የዝቅተኝነት ስሜት እንዳያዳብሩ ብቻ ነው፡፡ የኩሩ ህዝብም ልብ ቢሆን አንዴ የሀሰት የጭቆና ተረት ከተፈጠረለትና ልቡ ከተሰበረ ለመመለስ አስቸጋሪ ነው፡፡ እኔ የማውቀው ስለቅማንት ይህ ነው፡፡ ቅማንት ይባላሉ እንጅ በመሰረታዊ ነገር ከአማራ ጋር ምንም ልዩነት የላቸውም፡፡ ከዚህም የተነሳ በግንድ ዝርያቸው አማራ ናቸው እላለሁ፡፡ በጣም ጀግና ናቸው፡፡ የበታችነት ስሜት ፈጽሞ የሌለባቸው፡፡ ኩራትና ትምክህታቸው እንዴውም በተለምዶ አማራ ከሚባለው እኩል እንጅ የማያንስ፡፡ አንድ ሽህ አንድ መለያ ነጥቦች ቢደረደሩ በአንድ ሽህ ነገሮች አንድ ናቸው፡፡ ምናልባት ቅማንት እና አማራ የሚል ተለምዷዊ አጠራር ከመኖሩ ውጭ፡፡

በእርግጥ እስከ አጼ ዮሐንስ 4ኛ ድረስ እምነትና ባህላቸው ተጠብቆ ነው የኖሩት፡፡ ጎንደር ውስጥና በዙሪያዋም ሲኖሩ ምንም ጫና አልተደረገባቸውም፡፡ አጼ ዮሐንስ ግን አባ ዮሐንስ የተባለ መነኩሴ በማምጣት አስገድዶ ክርስትና እንዲነሱ አደረገ፤ አማርኛ ብቻ እንዲናገሩና ቅማንትኛ እንዲጠፋ አደረገ፡፡ የዛ በቅማንት ላይ ቀውስ ያመጣው ሰው ዛሬ ጋና ዮሐንስ በተባለ ቦታ ላይ (በጭልጋ መተማ መስመር) የመታሰቢያ ቤተክርስቲያን ተሰርቶለት ይገኛል፡፡ አያታቸው የጀመረውን ቅማንት የማጥፋት ሂደት ዛሬ ወያኔዎች እያፋጠኑት ነው፡፡ እንደወያኔ ህልም አማራ ጨርሶ ቢጠፋም ቅማንት መጥፋቱ አይቀርም፡፡ አማራ ጨርሶ ካልጠፋ እንኳ ትርፉ ለቅማንት ቂምና ቁርሾ ነው፡፡ አሁን ወያኔ እየተጠቀመበት ያለው ዘዴ አማራ የራሱን እጣቶች በራሱ እጣቶች እየቀረጠፈ እንዲበላ ማድረግ ነው፡፡ ቅማንት የሚለውን አሁን የሚራገብ የሀሰት ማንነት በመጠቀም ህዝቡን መከፋፈልና ማጥፋት ነው፡፡ ይህ አሁን የሚራገብ የውሸት ማንነት ለወያኔ በመሳሪያነት ብቻ የሚያገለግል ነው፡፡ ከዚህ በተቀረ ቅማንት በጎንደር ነገስታት በደል ሳይደርስበት እንደተከበረ ኖሯል፡፡ የዚህም ምስክሩ ህዝቡ ምንም አይነት ጎሳዊ ቅራኔ የሌለው እና የኩራት እና የጀግንነት መንፈሱ የተጠበቀ መሆኑ ነው፡፡ የተጨቆነ ህዝብ ድፍረትና ወኔ እንዲሁም የበላይነት ወይም የእኩልነት ስሜት አይኖረውም፡፡ ልበ ሰባራ ነው የሚሆነው፡፡ ቅማንት ግን ልበ ሙሉ እና ጀግና ነው፡፡ ይህም የዛሬው ባህሉና ባህርይው ያለፈውን ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር እንድንገነዘብ ያስችለናል፡፡

የመጀመሪያው የቅማንት ጥፋት ዘመቻ የተከፈተው በአጼ ዮሐንስ እንደሆነ አይተናል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በወያኔ ነው፡፡ የወያኔው ለየት የሚለው የማበጣበጥ እና ለወደፊቱ በሰላም የመኖርን እድል ፈተና ላይ የጣለ መሆኑ ነው፡፡ ማንም አእምሮ ያለው ሰው የአሁኑ አጀንዳ ለማንም እንደማይበጅ ያውቀዋል፡፡ ለዚህም የሚያሳዝነው ፊደል-ቀመስ የቅማንት ወጣቶች ከወያኔ ጋር አስረሽ ምች ማለታቸው ነው፡፡ በውሸት ፕሮፓጋንዳ ተነድተው ከወያኔ ጎን ተሰልፈዋል፡፡ በጥፋት እጅነትም የራሳቸውን ወገን እየበደሉ ናቸው፡፡ ይህ ያሳዝናል፡፡ በተለይ የጥንቱን ታሪክ ለሚያውቀወ ሰው ትልቅ በደል ነው እየተፈጸመ ያለው፡፡ የቅማንት ወጣቶችም የአሁኑ እቅስቃሴ አማራን ማለትም ራሳቸውን ለመከፋፈል እና ለማዳከም እንጅ ለእነሱ ታስቦላቸው እንዳልሆነ ይገንዘቡ፡፡ ለእነሱ እንዳልታሰበላቸው አንድ ነገር ልጠቁም፡፡ ወያኔ አጼ ቴዎድሮስ ቅማንት ነው ይላል፡፡ ይህን ማለቱ አላማው ቴዎድሮስ አማራ አይደለም የሚል እና የአማራን ስነልቡና መስበር ነው፡፡ እንደገና ዞር ይልና ደግሞ አማራ ቅማንትን ጨቆኖት ኖሯል ይላል፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ፡፡ ቴዎድሮስ ከታላላቆቹ የአማራ ነገስታት አንዱ ነው፡፡ ቴዎድሮስ ቅማንት ነው ማለት ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው ቅማንትን ከመጨቆን ጋር የሚገናኘው? ስለዚህ ቴዎድሮስ ነው የቅማንት ጨቋኝ? እንደዛ ከሆነ ቅማንት ነው ራሱን የጨቆነው ማለት ነው፡፡ ይህ ነው እግዲህ የወያኔ ስራ ሀሳዊነት መገለጫው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ቴዎድሮስ ቅማንት የመሆን እና ያለመሆኑ አይደለም፡፡ ቴዎድሮስ አማራ በመሆኑ ቅማንት ነው፡፡ ለምን ቢባል ቅማንት ራሱ አማራ ስለሆነ፡፡ እንዲያው የልማዱን አጠራር ብንጠቀም እንኳ እጅግ የታወቁት የቴዎድሮስ የጦር አለቆች በከፊል ቅማንቶች ነበረ፡፡ አንዱ ፊታውራሪ ገልሞ ነው፡፡ ይሁን እንጅ የወያኔ አላማ ቅማንት ብሎ የሚያስበውን ወገን መጥቀም አይደለም፡፡ ከፋፍሎ ማጥፋት ነው፡፡

ልብ ያለው ልብ ይበል…..
መለክ ሐራ ከቤተ አማራ
ጎንደር ቤተ አማራ