ክፉም በጎም የኛ ከሆነ የኛ ነው፤ ታሪክን ማካፈል ይቁም!
ደርግ አንድ ትውልድ አጥፍቷል ማለት አንድ ትውልድ አማራ ጠፍቷል ማለት ነው፡፡ ለብሄረሰብ ተዋጽኦ ብለን የምንደብቃት እውነት አትኖርም፡፡ ሶማልያ ዘምተው 20 አመት ሙሉ የተከማቸ የራሽያ የጦር መሳሪያ የዘነበባቸው አብዛኞች አማሮች፡፡ ኤርትራ ውስጥ ያለቁት አብዛኞቹ አማሮች፡፡ በቀይ ሽብር እየታደኑ የተጨረሱት ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ አማሮች፡፡ ፊውዳልና አድሀሪ ተብለው የተረሸኑት አማሮች፡፡ ወያኔንና ኢህዴንን ደብቃችኋል ተብለው የተረሸኑት አማሮች፡፡ ቆሎ ሳይቀር ቆነጠርክ ተብለው የተረሸኑት አማሮች፡፡ እገሌ ሽፍታ ነው እየተባሉ በየሰበቡ የተረሸኑት አማሮች፡፡
ቤተ አማሮች ሆይ የአማራ የሆነን ሁሉ በግልጽ ደፍራችሁ የአማራ ነው በሉ፡፡ ያልሆነውንም እንዲሁ፡፡ ለመወደድ ብለን ክፉውንም ሆነ በጎውን “የእናንተም እኮ ነው” ማለት እናቁም፡፡ ክፉም ነገር ካለን የራሳችን ነው፡፡ በጎም ነገራችን የራሳችን ብቻ ነው፡፡ ታሪክ እውነት ስለሆነ በውሸት ማናቸውንም ታሪካችንን ለማንም አናክፍልም፡፡በዋጋ የገዛነውን ታሪክ በነጻ አናድልም፡፡ ሊያውም “ያንተም ድርሻ አለበት” ስንለው ለሚያላግጥብን ሁሉ፡፡ በታሪክ ያልነበረውን ሁላ “ነበርክ እኮ” እያልን ስናቆላምጥ ነው የኖርነው፡፡ ካሁን በኋላ ያልነበረ አልነበረም፡፡ የኛ የሆነ ሁሉ የኛ ብቻ ነው፡፡ ማንም ተገለልኩ ምናምን ብሎ ቢከፋው የራሱ ጉዳይ ነው፡፡
እኔ በኖርኩባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች ሁሉ ያጋጠሙኝ የሌላ ብሄረሰብ ተወላጆች “የአማራ መሬት ለሱዳን ተሰጠ” እንጅ “የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን ተሰጠ” ሲሉ ሰምቻቸው አላውቅም፡፡ ይባስ ብለው “መሬታችሁን አታስመልሱም እንዴ” እያሉ ይቀልዱብኛል፡፡ በዚህ ምን ትዝ ይለኛል ታዲያ “አገራችን ተደፈረች” ብለው ሆ ብለው ዛላምበሳና ምናምን ሄደው የሰው ድንጋይ አገር እስከ ህይወታቸው አፈር ለበሰው የቀሩት አማሮች፡፡ ከሁዋላ ወያኔ ከፊት ሻእብያ ሆነው አፈር አልብሰዋቸው የቀሩት አማሮች ትዝ ይሉኛል፡፡ ይህ በሞታችን ህይወቱን የቀጠልንለት ወያኔ ግን “መሬታችን ሰጠህ” ብለን እንድንናገረው አይፈቅድም፤ ጭራሽ ወንጀል ያደርገዋል፡፡ እንደዛሬው ሀሳቤን የሚጋሩኝ የአማራ ልጆች ሳላገኝ በዚህና በሌላ ብዙ ነገር ብቻየን ስበሽቅ ነው የኖርኩት፡፡ አሁን ብቻችን አንበሽቅም፡፡ ቢያንስ አብረን ነን፡፡ በዚህ ደስ ይለኛል፡፡
መለክ ሐራ ከቤተ አማራ